የኢያሪኮ ውድቀት
103 ቁጥሮች5አማርኛኢያ 2:1-24
1የነዌም ልጅ ኢያሱ፦ ሄዳችሁ ምድሪቱንና ኢያሪኮን እዩ ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ። ሄዱም፤ ረዓብም ወደሚሉአት ጋለሞታ ቤት ገቡ፥ በዚያም አደሩ።
2የኢያሪኮም ንጉሥ፦ እነሆ፥ ሰዎች ከእስራኤል ልጆች አገሩን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ፡ ሲባል ወሬ ሰማ።
3የኢያሪኮም ንጉሥ፦ አገሩን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን ወደ ቤትሽም የገቡትን ሰዎች አውጪ፡ ብሎ ወደ ረዓብ ላከ።
4ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም፦ አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፥ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤
5በሩም ሲዘጋ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፤ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፤ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ታገኙአቸውማላችሁ፡ አለች።
6እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፤ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር።
7ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ አሳደዱአቸው፤ እሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተቈለፈ።
8እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች።
9ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ።
10ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል።
11ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተንሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም።
12አሁንም፥ እባካችሁ፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ ሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድትሠሩ፥
13አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ እንድታድኑ፥ ሰውነታችንንም ከሞት እንድታድኑ።
14ሰዎቹም፦ ይህን ነገራችንን ባትገልጪ ነፍሳችን በነፍሳችሁ ፋንታ ለሞት ይሆናል፤ እግዚአብሔርም ምድሪቱን በሰጠን ጊዜ ከአንቺ ጋር ቸርነትንና እውነትን እናደርጋለን፡ አሉአት።
15ቤትዋም በከተማ ቅጥር የተጠጋ ነበረና፥ እርስዋም በቅጥሩ ላይ ተቀምጣ ነበርና ከመስኮቱ በገመድ አወረደቻቸው።
16እርስዋም፦ አሳዳጆቹ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፤ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፤ ኋላም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ፡ አለቻቸው።
17ሰዎቹም አሉአት፦ እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን።
18እነሆ፥ እኛ ወደ አገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፤ አባትሽንም እናትሽንም ወንድሞችሽንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ።
19ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን አንድ እጅ ቢነካው ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል።
20ይህንን ነገራችንን ግን ብትገልጪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን።
21እርስዋም፦ እንደ ቃላችሁ ይሁን፡ አለች፤ ሰደደቻቸውም እነርሱም ሄዱ፤ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው።
22እነርሱም ሄደው ወደ ተራራው ደረሱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፤ አሳዳጆቹም በመንገዱ ሁሉ ፈልገው አላገኙአቸውም።
23ሁለቱም ሰዎች ተመለሱ፥ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፤ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት።
24ኢያሱንም፦ በእውነት እግዚአብሔር አገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ በአገሩም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በፊታችን ይቀልጣሉ፡ አሉት።
ኢያ 3:1-17
1ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እርሱና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሰጢም ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ።
2ከሦስት ቀንም በኋላ አለቆች በሰፈሩ መካከል አለፉ።
3ሕዝቡን፦ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት።
4በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን፤ በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ፡ ብለው አዘዙ።
5ኢያሱም ሕዝቡን፦ ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ፡ አለ።
6ኢያሱም ካህናቱን፦ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ ብሎ ተናገራቸው፤ የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት አለፉ።
7እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ሁሉ ዓይን ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ።
8አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት፦ በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ ብለህ እዘዝ፡ አለው።
9ኢያሱም ለእስራኤል ልጆች፦ ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፡ አለ።
10ኢያሱም አለ፦ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደ ሆነ፥ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን ኬጢያዊውንም ኤዊያዊውንም ፌርዛዊውንም ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈጽሞ እንዲያወጣ በዚህ ታውቃላችሁ።
11እነሆ፥ የምድር ሁሉ ጌታ ቃል ኪዳን ታቦት በፊታችሁ ወደ ዮርዳኖስ ያልፋል።
12አሁንም ከእስራኤል ነገዶች አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጡ፤ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ይሁን።
13እንዲህም ይሆናል፤ የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግር ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ ከላይ የሚወርደው የዮርዳኖስ ውኃ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል።
14እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር።
15እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ፥ ታቦቱንም የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ፥
16ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ።
17የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፥ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ።
ኢያ 4:1-24
1እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔርም ኢያሱን፦
2ከሕዝቡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጥና፦
3በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሡ፤ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው ብለህ እዘዛቸው፡ አለው።
4ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች ያዘጋጃቸውን አሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ።
5ኢያሱም አላቸው፦ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል እለፉ፤ ከእናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም።
6ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል፤ ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን፦ የእነዚህ ድንጋዮች ነገር ምንድር ነው? ብለው ሲጠይቁአችሁ፥
7እናንተ፦ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፤ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ፥ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘላለም መታሰቢያ ይሆናሉ፡ ትሉአቸዋላችሁ።
8የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዘ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን እንደ ተናገረው በእስራኤል ነገድ ቍጥር ከዮርኖስ መካከል አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደሚያድሩበት ስፍራ ወሰዱ፥ በዚያም አኖሩአቸው።
9ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎችን አሥራ ሁለት ድንጋዮች ተከለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።
10ሙሴም ኢያሱን እንዳዘዘው ሁሉ፥ እግዚአብሔር ኢያሱን ለሕዝቡ እንዲነግር ያዘዘው ነገር ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ነበርና፤ ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ።
11ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ እያዩ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ ተሻገሩ።
12ሙሴም እንዳዘዛቸው የሮቤል ልጆች፥ የጋድም ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ተሰልፈው በእስራኤል ልጆች ፊት ተሻገሩ።
13አርባ ሺህ ያህል ሰዎች ጋሻና ጦራቸውን ይዘው ለሰልፍ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ።
14በዚያም ቀን እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ አደረገው፤ ሙሴንም እንደ ፈሩ በዕድሜው ሁሉ ፈሩት።
17ኢያሱም ካህናትን፦ ከዮርዳኖስ ውጡ፡ ብሎ አዘዛቸው።
18የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ከዮርዳኖስ መካከል በወጡ ጊዜ፥ የካህናቱም እግር ጫማ ደረቅ መሬት መርገጥ በጀመረ ጊዜ፥ የዮርዳኖስ ውኃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፥ ቀድሞም እንደ ነበረ በዳሩ ሁሉ ላይ ሄደ።
19ሕዝቡም በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን ከዮርዳኖስ ወጡ፥ በኢያሪኮም ዳርቻ በምሥራቅ በኩል በጌልገላ ሰፈሩ።
20ከዮርዳኖስም ውስጥ የወሰዱአቸውን እነዚያን አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ኢያሱ በጌልገላ አቆማቸው።
21ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ አባቶቻቸውን፦ እነዚህ ድንጋዮች ምንድር ናቸው? ብለው ሲጠይቁ፥
22ለልጆቻችሁ እንዲህ ብላችሁ ታስታውቃላችሁ፦ እስራኤል ይህን ዮርዳኖስን በደረቅ ተሻገረ፤
23እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ።
24ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድትፈሩ ነው።
ኢያ 5:1-15
1እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል የነበሩት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ፥ በባሕሩም አጠገብ የነበሩ የከነዓናውያን ነገሥት ሁሉ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት የዮርዳኖስን ውኃ እስኪሻገሩት ድረስ እንዳደረቀ በሰሙ ጊዜ፥ ልባቸው ቀለጠ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ነፍስ ከዚያ ወዲያ አልቀረላቸውም።
2በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ኢያሱን፦ የባልጩት መቍረጫ ሠርተህ የእስራኤልን ልጆች ሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው፡ አለው።
3ኢያሱም የባልጩት መቍረጫ ሠርቶ የግርዛት ኮረብታ በተባለ ስፍራ የእስራኤልን ልጆች ገረዘ።
4ኢያሱ የገረዘበትም ምክንያት ይህ ነው፤ ከግብፅ የወጡት ሕዝብ ወንዶች ሰልፈኞች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞቱ።
5የወጡት ሕዝብ ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ነገር ግን ከግብፅ በወጡበት መንገድ በምድረ በዳ የተወለዱት ሕዝብ ሁሉ አልተገረዙም ነበር።
6እግዚአብሔርም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው የማለላቸው፥ ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርንም ቃል ያልሰሙ፥ እነዚያ ሰልፈኞች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር።
7ልጆቻቸውን በእነርሱ ፋንታ አስነሣ፥ እነዚህንም ኢያሱ ገረዛቸው፤ በመንገድ ሳሉ ስላልገረዙአቸው ሸለፈታሞች ነበሩና።
8ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተገረዙ ጊዜ እስኪድኑ ድረስ በሰፈር ውስጥ በየስፍራቸው ተቀመጡ።
9እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ፡ አለው፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ።
10የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፤ ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በኢያሪኮ ሜዳ ፋሲካ አደረጉ።
11ከፋሲካውም በኋላ በነጋው የምድሪቱን ፍሬ የቂጣ እንጎቻ ቆሎም በዚያው ቀን በሉ።
12በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ።
13እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው።
14እርሱም፦ አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ፡ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፦ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው።
15የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን፦ አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፡ አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ።
ኢያ 6:1-25
1ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርስዋ የሚገባ ከእርስዋም የሚወጣ ማንም አልነበረም።
2እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፦ ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ።
3ሰልፈኞቻችሁ ሁሉ ከተማይቱን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ።
4ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ።
5ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱንም ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ይገባባታል።
6የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፦ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ፡ አላቸው።
7ሕዝቡንም፦ ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ሰልፈኞችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ፡ አለ።
8ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር።
9ሰልፈኞቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የቀረውም ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር።
10ኢያሱም ሕዝቡን፦ እኔ፦ ጩኹ፡ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታንሡ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ፡ ብሎ አዘዛቸው።
11እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ።
12ኢያሱም ማለዳ ተነሣ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ።
13ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ሰልፈኞቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር።
14በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ።
15በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፥ እንደዚህም ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ።
16በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን አለ፦ እግዚአብሔር ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ።
17ከተማይቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱ ረዓብ ከእርስዋም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ።
18እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደ ሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁትማላችሁ።
19ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።
20ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ።
21በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።
22ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች፦ ወደ ጋለሞታይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ፡ አላቸው።
23ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው።
24ከተማይቱንም በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አደረጉት።
25ኢያሪኮን ሊሰልሉ ኢያሱ የሰደዳቸውንም መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተ ሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርስዋም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች።