የመጨረሻው እራት

14 ቁጥሮችአማርኛ

ማር 14:12-25

12ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ፦ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ?” አሉት።

13ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው፦ “ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤

14ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ፦ ‘መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል’ በሉት።

15እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።”

16ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ።

17በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ።

18ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ፦ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል፡” አለ።

19እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም፦ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር።

20እርሱም መልሶ አላቸው፦ “ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው።

21የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።”

22ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ “እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፡” አለ።

23ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።

24እርሱም አላቸው፦ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው።

25እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም።”