የሚቃጠል ቡሽ
37 ቁጥሮች2አማርኛዘጸ 3:1-22
1ሙሴም የዮቶርን የአማቱን የምድያምን ካህን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ ወደ ምድረ በዳ ዳርቻም በጎቹን ነዳ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ።
2የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ።
3ሙሴም፦ “ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ ራእይ ልይ፡” አለ።
4እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ፦ “ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ፡” አለ።
5እርሱም፦ “እነሆኝ፡” አለ። “ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ፡” አለው።
6ደግሞም፦ “እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፡” አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ።
7እግዚአብሔርም አለ፦ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤
8ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ።
9አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ።
10አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።”
11ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው።
12እርሱም፦ በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ፡ አለ።
13ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ፡ ባልሁም ጊዜ፦ ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው።
14እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “ያለና የሚኖር” እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ “ያለና የሚኖር፡ ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ፡” አለው።
15እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው’።”
16ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ፦ “እግዚአብሔር የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም የይስሐቅም የያዕቆብም አምላክ፦ ‘መጐብኘትን ጐበኘኋችሁ፥ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤
17ከግብፅም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ አልሁ፡’ ብሎ ተገለጠልኝ፡ በላቸው።
18እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትገባላችሁ፦ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ አሁንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንሠዋ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንሂድ፡’ ትሉታላችሁ።
19ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር ትሄዱ ዘንድ የግብፅ ንጉሥ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ።
20እኔም እጄን እዘረጋለሁ፥ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል።
21በግብፃውያንም ፊት ለዚህ ሕዝብ ሞገስን እሰጣለሁ፤ እንዲህም ይሆናል፤ በሄዳችሁ ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም፤
22ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤትዋ በቤትዋም ካለችው ሴት የብር ዕቃ የወርቅ እቃ ልብስም ትለምናለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይ ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም ትበዘብዛላችሁ።”
ዘጸ 4:1-17
1ሙሴም መለሰ፦ “እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም፦ ‘እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም፡’ ይሉኛል፡” አለ።
2እግዚአብሔርም፦ “ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት?” አለው። እርሱም፦ “በትር ናት፡” አለ።
3“ወደ መሬት ጣላት፡” አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፥ እባብም ሆነች፤ ሙሴም ከእርሷ ሸሸ።
6እግዚአብሔርም ደግሞ፦ “እጅህን ወደ ብብትህ አግባ፡” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ ባወጣትም ጊዜ እነሆ፥ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች።
7እርሱም፦ “እጅህን ወደ ብብትህ መልስ፡” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፥ ከብብቱም ባወጣት ጊዜ እነሆ ተመልሳ ገላውን መሰለች።
8ደግሞም አለው፦ “እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ነገር ባይሰሙ፥ የሁለተኛይቱን ምልክት ነገር ያምናሉ።
9እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፥ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።”
10ሙሴም እግዚአብሔርን፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም።”
11እግዚአብሔርም፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?
12እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ፡” አለው።
13እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ፡” አለ።
14የእግዚአብሔርም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ፦ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደህና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል።
15አንተም ትናገረዋለህ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ።
16እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም በእግዚአብሔር ፋንታ ትሆንለታለህ።
17ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ።”