የ 4000 ሰዎች መመገብ

21 ቁጥሮች2አማርኛ

ማቴ 14:13-21

13ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት።

14ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ።

15በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት፡” አሉት።

16ኢየሱስም፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም፡” አላቸው።

17እነርሱም፦ “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም” አሉት።

18እርሱም፦ “እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ” አላቸው።

19ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ።

20ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ።

21ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር።

ማቴ 14:22-33

22ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።

23ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።

24ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር።

25ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።

26ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፦ “ምትሐት ነው፡” ብለው ታወኩ፥ በፍርሃትም ጮኹ።

27ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና፦ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፡” አላቸው።

28ጴጥሮስም መልሶ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው።

29እርሱም፦ “ና” አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።

30ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ “ጌታ ሆይ፥ አድነኝ፡” ብሎ ጮኸ።

31ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ “አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ?” አለው።

32ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ።

33በታንኳይቱም የነበሩት፦ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።