የደረቁ አጥንቶች ሸለቆ
14 ቁጥሮችአማርኛሕዝ 37:1-14
1የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ።
2በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆም፥ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር።
3እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን? አለኝ። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ፡ አልሁ።
4እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር፡ እንዲህም በላቸው፦ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ።
5ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
6ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
7እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ።
8እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም።
9እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው፡ በል፡ አለኝ።
10እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፦ አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል፡ ብለዋል።
12ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ፥ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ።
13ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
14መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።