የያዕቆብ መሰላል

13 ቁጥሮችአማርኛ

ዘፍ 28:10-22

10ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ።

11ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ።

12ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር።

13እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፦ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤

14ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ።

15እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።”

16ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ፦ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር፡” አለ።

17ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ “ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።”

18ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት።

19ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ።

20ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፦ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥

21ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤

22ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ።”