1ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤
2አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦
3“በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
4የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።
5የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።
6ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።
7የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።
8ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
9የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
10ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
11“ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
12ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
13“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
14“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።
15መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።
16መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።
17“እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።
18እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።
19እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል።
20እላችኋለሁና፦ ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።
21“ለቀደሙት፦ ‘አትግደል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ ‘የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል’።
22እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም፦ ‘ጨርቃም’ የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ‘ደንቆሮ’ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።
23“እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥
24በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።
25“አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤
26እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።
27“ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
28እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።
29ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና።
30ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና።
31‘ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት’ ተባለ።
32እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።
33“ደግሞ ለቀደሙት፦ ‘በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ፡’ እንደተባለ ሰምታችኋል።
34እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤
35በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤
36በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና።
37ነገር ግን ቃላችሁ ‘አዎን አዎን’ ወይም ‘አይደለም አይደለም’ ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው።
38‘ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ፡’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
39እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤
40እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤
41ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ።
42ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል።
43‘ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ፡’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
44እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።
46የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?
47ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?
48እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።”