የማቴዎስ ወንጌል 5

AMHNIVአማርኛ48 ጥቅሶች7:32 አዳምጥ
አዳምጥ 7:32 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ብዙ ሕዝብ እንደ ተሰበሰበ ባየ ጊዜ፣ ወደ ተራራ ወጣና ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ መጡ።

2እንዲህም እያለ ያስተምራቸው ጀመር፤

3“በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።

4የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና።

5የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።

6ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና።

7ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና።

8ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና።

9ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና።

10ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።

11“ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ።

12በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳደዋቸዋልና።

13“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላልን? ወደ ውጪ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ጥቅም አይኖረውም።

14“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤

15ሰዎችም መብራት አብርተው ከዕንቅብ ሥር አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ።

16እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።

17“ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።

18እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም።

19ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዛት አነስተኛዪቱን እንኳን ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል።

20ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም።

21“ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤

22እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል።

23“ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣

24መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።

25“የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ በወህኒም እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ።

26እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።

27“ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

28እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል።

29ቀኝ ዓይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።

30ቀኝ እጅህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።

31“ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

32እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በላዩ ላይ ስታመነዝር ካላገኛት በስተቀር፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውን ሴት ያገባም እንዳመነዘረ ይቈጠራል።

33“ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በእግዚአብሔር ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

34እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤

35በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና

36በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና።

37ስለዚህ ስትነጋገሩ ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ፣ ‘አዎን’፤ አይደለም፣ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነውና።

38“ ‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

39እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጒንጭህን ደግሞ አዙርለት።

40አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው።

41አንድ ሰው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ።

42ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚሻውን ፊት አትንሣው።

43“ ‘ወዳጅህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

44እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ።

45እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።

46የሚወዷችሁን ብቻ የምትወዱ ከሆነ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?

47ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?

48ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።”

ማብራሪያ

5:1,2 በቃሉ ህግ መሠረት ከክርስቶስ ደስታን የማይሹ ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ደስታን አያገኙም። እርሱም ሊጠሉት የሚገባው ክፉ ነገር ምን እንደሆነና ሊፈልጉትና ሊበዙበት የሚገባው መልካም ነገር ምን እንደሆነ አስተማራቸው።

5:3-12 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እዚህ ላይ የተባረኩ ሰዎችን ስምንት ባህሪያትን ይሰጣል፤ እነዚህም የአንድ ክርስቲያን ዋነኛ ጸጋዎችን ለእኛ ያሳያሉ።

1. በመንፈስ ድሆች የሆኑ የተባረኩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሁኔታቸው ዝቅተኛ ሲሆን አእምሮአቸውን ከሁኔታቸው ጋር ያስማማሉ። በራሳቸው ዓይን ትሑቶችና ዝቅተኞች ናቸው። ጉድለታቸውን ያያሉ፣ ጥፋታቸውን ያዝናሉ፣ እና ቤዛን ይናፍቃሉ። የጸጋው መንግሥት የእነዚህ ነው፤ የክብር መንግሥትም ለእነርሱ ነው። 2. የሚያለቅሱ የተባረኩ ናቸው። እዚህ ላይ የታሰበው፣ እውነተኛ ንስሐን፣ ንቃትን፣ ትሑት ልብን፣ እና በክርስቶስ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ምሕረት ለመጽደቅ ዘወትር መታመንን የሚሠራ፣ ከቀሪው ክፋት ለማንጻት መንፈስ ቅዱስን ዘወትር ከመፈለግ ጋር የተያያዘ መለኮታዊ ኀዘን ይመስላል። ሰማይ የጌታችን ደስታ ነው፤ መንገዳችን በእንባ ሸለቆ የሚያልፍበት የደስታ ተራራ ነው። እንዲህ ያሉ አዛኞች በአምላካቸው ይጽናናሉ። 3. የዋሆች የተባረኩ ናቸው። የዋሆች ማለት በጸጥታ ለእግዚአብሔር የሚገዙ፣ ስድብን ሊሸከሙ የሚችሉ፣ ዝም የሚሉ ወይም ለስላሳ መልስ የሚመልሱ፣ እና ምንም ነገር በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል ሲያቅታቸው እንኳ በትዕግሥታቸው የራሳቸውን ነፍሶች የሚጠብቁ ናቸው። እነዚህ የዋሆች በዚህ ዓለምም ቢሆን የተባረኩ ናቸው። የዋህነት በዚህ ዓለምም ሀብትን፣ ምቾትንና ደህንነትን ያበረታታል። 4. ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ የተባረኩ ናቸው። ጽድቅ እዚህ ላይ ሁሉንም መንፈሳዊ በረከቶች ይወክላል። እነዚህ በረከቶች በክርስቶስ ጽድቅ ለእኛ የተገዙ ሲሆኑ፣ በእግዚአብሔር ታማኝነት የተረጋገጡ ናቸው። ለመንፈሳዊ በረከቶች ያለን ፍላጎት ቅን መሆን አለበት። ምንም እንኳ ለጸጋ ያሉ ሁሉም ፍላጎቶች ጸጋ ባይሆኑም፣ እንደዚህ ያለ ፍላጎት ግን በእግዚአብሔር ራሱ የሚነሳ ፍላጎት ነው፣ እርሱም የገዛ እጆቹን ሥራ አይተውም። 5. መሐሪ የሆኑት የተባረኩ ናቸው። የራሳችንን መከራ በትዕግሥት ከመሸከም ባለፈ፣ በችግር ውስጥ ያሉትን ለመርዳት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን። የሌሎችን ነፍሳት ማዘንና መርዳት አለብን፤ በኃጢአት ውስጥ ያሉትን ማዘንና እንደ እሳት ፍንጣሪዎች ከቃጠሎው ለመንጠቅ መፈለግ አለብን። 6. በልባቸው ንጹሓን የሆኑ የተባረኩ ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና። እዚህ ላይ ቅድስናና ደስታ ሙሉ በሙሉ ተብራርተውና ተጣምረው ቀርበዋል። ልብ በእምነት መነጻትና ለእግዚአብሔር መጠበቅ አለበት። «አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ በውስጤ ንጹሕ ልብ ፍጠር።» ንጹሓን ካልሆኑ በቀር ማንም እግዚአብሔርን ለማየት ብቁ አይደለም፣ ንጹሕ ላልሆነ ሰውም ሰማይ ደስታ አይሆንም። እግዚአብሔር ክፋታቸውን ሊመለከት እንደማይችል፣ እነርሱም ንጽሕናውን ሊመለከቱ አይችሉም። 7. ሰላም ፈጣሪዎች የተባረኩ ናቸው። እነርሱ ሰላምን ይወዳሉ፣ ይፈልጋሉ፣ በእርሱም ይደሰታሉ፤ ጸጥ ለመሆንም ይተጋሉ። ሰላም እንዳይፈርስ ይጠብቃሉ፣ ሲፈርስም ይመልሱታል። ሰላም ፈጣሪዎች የተባረኩ ከሆኑ፣ ሰላም አፍራሾች ወዮላቸው! 8. ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ የተባረኩ ናቸው። ይህ አባባል ለክርስትና ልዩ ነው፤ ከቀሩት ሁሉ በስፋት አጽንኦት ተሰጥቶበታል። ሆኖም በመከራችን ውስጥ ከእግዚአብሔር በረከትን ሊያስገኝ የሚችል ምንም ነገር የለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእርሱ የሚያጡት፣ ሕይወታቸውን ራሱን እንኳ ቢሆን፣ በመጨረሻ በእርሱ ምክንያት አይጎዱም ያደርጋል። የተባረከ ኢየሱስ! መርሆዎችህ ከዚህ ዓለም ሰዎች መርሆዎች እንዴት ይለያያሉ! እነርሱ ትዕቢተኞችን ደስተኛ ይሏቸዋል፣ ሐሴት የሚያደርጉትን፣ ባለጸጎችን፣ ኃያላኖችንና አሸናፊዎችን ያደንቃሉ። ከጌታ ዘንድ ምሕረትን እናግኝ፤ ልጆቹ ተብለን እንታወቅ፣ መንግሥቱንም እንውረስ። በእነዚህ ደስታዎችና ተስፋዎች ዝቅተኛ ወይም አሳማሚ ሁኔታዎችን በደስታ ልንቀበል እንችላለን።

5:13-16 እናንተ የምድር ጨው ናችሁ። የሰው ልጅ በድንቁርናና በክፋት ውስጥ ወድቆ፣ ለመበስበስ የተዘጋጀ ትልቅ ክምር ይመስል ነበር፤ ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱን በሕይወታቸውና በትምህርታቸው በእውቀትና በጸጋ እንዲያጣፍጡት ላካቸው። ሊሆኑ የሚገባቸው ካልሆኑ ግን፣ ጣዕሙን እንደጠፋ ጨው ናቸው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6