ትንቢተ ሆሴዕ 8

AMHEVGአማርኛ14 ጥቅሶች2:02 አዳምጥ
አዳምጥ 2:02 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፤ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ንስር ይመጣል።

2እነርሱም፦ “አምላክ ሆይ፥ እኛ እስራኤል አወቅንህ፡” ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ።

3እስራኤል ደግነትን ጥሎአል፤ ጠላትም ያሳድዱታል።

4ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም አደረጉ፥ እኔም አላወቅሁም፤ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው፤ ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ።

5ሰማርያ ሆይ፥ እምቦሳህን፤ ጥሎአል፤ ቍጣዬ በላያቸው ነድዶአል፤ እስከ መቼ ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም?

6ይህ ደግሞ ከእስራኤል ዘንድ ነው፤ ሠራተኛ ሠራው፥ እርሱም አምላክ አይደለም፤ የሰማርያም እምቦሳ ይቈራረጣል።

7ነፍስን ዘርተዋል፥ ዐውሎ ነፍስንም ያጭዳሉ፤ አገዳ የለውም፥ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም እንግዶች ይበሉታል።

8እስራኤል ተውጦአል፥ በአሕዛብም መካከል ዛሬ እንደ ረከሰ ዕቃ ሆኖአል።

9ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም ወዳጆቹን በእጅ መንሻ ገዛ።

10ነገር ግን ለአሕዛብ እጅ መንሻ ቢሰጡ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ ይደክማሉ።

11ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያ አብዝቶአልና መሠዊያ ለኃጢአት ይሆንለታል።

12የሕጌን ብዛት ጽፌለታለሁ፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጥረውታል።

13መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፤ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፤ እነርሱም ወደ ግብፅ ይመለሳሉ።

14እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችንም ትበላለች።

ማብራሪያ

8:1-4 እስራኤል በጭንቀት በተጫነች ጊዜ ከእግዚአብሔር ጥበቃን ይማፀኑ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ቸል ይባል ነበር። ‹አምላኬ ሆይ፣ አውቅሃለሁ› ብሎ ማለት፣ ‹አምላኬ ሆይ፣ እወድሃለሁ፣ አገለግልሃለሁ፣ አንተንም ብቻ እጠጋለሁ› ብለን ለመናገር ካልቻልን፣ ምንስ ጥቅም ይኖረዋል?

8:5-10 ጣዖታትን በማምለክ ብዙ፣ ሰላምና ድልን ለራሳቸው ተስፋ አድርገው ነበርና፥ ነገር ግን ተስፋዎቻቸው ከንቱ ሆኑ። የዘሩት ግንድም ቅጠልም የለውም፥ ወይም ቢኖረውም እንኳን ቡቃያው ፍሬ አይሰጥም፤ በውስጣቸው ምንም አልነበረም። የጨለማ ሥራዎች ፍሬ የለሾች ናቸው፤ ይልቁንም የእነዚያ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነው። የኃጢአተኞች ተስፋ ያታልላቸዋል፥ ትርፋቸውም ወጥመድ ይሆናል። በአደጋ ጊዜ፥ በተለይም በፍርድ ቀን፥ ሥጋዊ ዘዴዎች ሁሉ ይከሽፋሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6