1እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ።
2ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። እግዚአብሔርን በድለዋልና፥
3ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ስድሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ከግብፅ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ።
4በይሁዳም የነበሩትን ምሽጎች ከተሞች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ።
5ነበዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።
6የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ፦ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፡ ብለው ሰውነታቸውን አዋረዱ።
7እግዚአብሔርም ሰውነታቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል፦ ሰውነታቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፥ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም፤
8ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለምድር ነገሥታት መገዛትን ያውቁ ዘንድ ይገዙለታል ሲል ወደ ሸማያ መጣ።
9የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ።
10ንጉሡም ሮብዓም በእነርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፥ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቃ እጅ አኖራቸው።
11ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፥ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር።
12ሰውነቱንም ባዋረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ነገር ተገኘ።
13ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች።
14እግዚአብሔርንም ይሻ ዘንድ ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ።
15የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ።
16ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።