1ኛ ቆሮንቶስ 15

AMHEVGአማርኛ57 ጥቅሶች7:33 አዳምጥ
አዳምጥ 7:33 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤

2በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ።

3እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን፡ ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፦ “መጽሐፍ እንደሚል፡ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥

4ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል፡ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥

5ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤

6ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤

7ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤

8ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።”

9እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤

10ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።

11እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ።

12ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን፡ ከእናንተ አንዳንዶቹ፦ “ትንሣኤ ሙታን የለም፥” እንዴት ይላሉ?

13ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤

14ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤

15ደግሞም፦ “ክርስቶስን አስነሥቶታል፤” ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም።

16ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤

17ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ።

18እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ።

19በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።

20አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።

21ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና።

22ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።

23ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤

24በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።

25ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።

26የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤

27ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፦ “ሁሉ ተገዝቶአል፡” ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው።

28ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።

29እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው?

30እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው?

31በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ።

32እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ።

33አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።

34በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።

35ነገር ግን ሰው፦ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ?“ የሚል ይኖር ይሆናል።

36አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤

37የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤

38እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል።

39ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው።

40ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው።

41የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና።

42የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤

43በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤

44ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ።

45እንዲሁ ደግሞ፦ “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።

46ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም።

47የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።

48መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው።

49የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።

50ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ “ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።”

51እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።

53ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።

54ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ “ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።

55ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?

56የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤

57ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።

58ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።

ማብራሪያ

፩፭፥፩-፲፩ ትንሣኤ የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ከመቃብር ባሻገር ያለውን ሕልውናችንን ያመለክታል። የሐዋርያው ትምህርት ፈለግ በፈላስፋዎች ትምህርት ሁሉ ውስጥ ሊገኝ አይችልም። የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ትምህርት የክርስትና መሠረት ነው። ይህን ካስወገድነው፣ የዘላለም ተስፋዎቻችን ሁሉ በአንዴ ይወድቃሉ። ክርስቲያኖች በፈተና ቀን የሚቆሙትና ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የሚጠበቁት ይህን እውነት አጥብቀው በመያዝ ነው። በወንጌል እምነት ውስጥ ካልጸናን በቀር፣ በከንቱ እናምናለን። ይህ እውነት በብሉይ ኪዳን ትንቢቶች የተረጋገጠ ሲሆን፣ ብዙዎችም እርሱ ከሞት ከተነሳ በኋላ ክርስቶስን አዩ። ይህ ሐዋርያ እጅግ ጸጋ የሞላበት ነበር፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ስለ ራሱ ትሑት አስተሳሰብ ነበረው፣ እርሱም ይገልጸው ነበር። ኃጢአተኞች በመለኮታዊ ጸጋ ወደ ቅዱሳን ሲለወጡ፣ እግዚአብሔር የቀድሞ ኃጢአቶቻቸውን ትዝታ ትሑት፣ ታታሪና ታማኝ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በእርሱ የነበረውን ውድ ነገር ሁሉ ለመለኮታዊ ጸጋ ያደርጋል። እውነተኛ አማኞች፣ ጌታ ለእነርሱ፣ በእነርሱ ውስጥና በእነርሱ አማካይነት ያደረገውን ቢያውቁም፣ ጠቅላላ ምግባራቸውንና ግዴታዎቻቸውን ሲመለከቱ፣ እንደ እነርሱ ምንም የማይረባ እንደሌለ እንዲሰማቸው ይደረጋሉ። ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱም የተሰቀለው፣ ከዚያም ከሙታን የተነሳው፣ የክርስትና ሁሉ እምብርትና ይዘት እንደሆነ ያምናሉ። ሁሉም ሐዋርያት በዚህ ምስክርነት ተስማምተዋል፤ በዚህ እምነት ኖረዋል፣ በዚህም እምነት ሞተዋል።

፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፥፲፪-፲፱ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ ካሳየ በኋላ፣ ሐዋርያው ትንሣኤ የለም ለሚሉ ሰዎች መልስ ይሰጣል። ክርስቶስ ባልተነሳ ኖሮ፣ ጽድቅ ወይም መዳን አይኖርም ነበር። እርሱ አሁንም በሙታን ዘንድ ቢገኝስ፣ በክርስቶስ ላይ ያለው እምነት ከንቱና ዋጋ ቢስ መሆኑ አይቀርም ነበርን? የሥጋ ትንሣኤ ማስረጃ የጌታችን ትንሣኤ ነው። ክርስቶስ ባልተነሳ ኖሮ፣ በእምነት የሞቱትም እንኳ በኃጢአታቸው የጠፉ ይሆኑ ነበር።

በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ እንደ ቤዛ በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ፤ በእርሱም በኩል ለቤዛነትና ለመዳን ተስፋ አላቸው። ነገር ግን ትንሣኤ ወይም የወደፊት ምንዳ ከሌለ፣ በእርሱ ያላቸው ተስፋ ለዚህ ሕይወት ብቻ የተወሰነ ይሆናል። በተለይም ሐዋርያት በጻፉበት ጊዜና ሁኔታ፣ ክርስቲያኖች በሁሉም ዘንድ የተጠሉና የተሳደዱ ስለነበሩ፣ ከሌሎቹ ሰዎች ሁሉ የባሰ ሁኔታ ውስጥ ይሆኑ ነበር። ነገር ግን እንዲህ አይደለም፤ እነርሱ በሁሉም ችግሮቻቸውና ፈተናዎቻቸው መካከል፣ እጅግ በከፋ ስደት ጊዜም ቢሆን፣ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ የጸና መጽናናትን ያገኛሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6