የኢየሱስን እግር ማጠብ
27 ቁጥሮች2አማርኛሉቃ 7:36-50
36ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ።
37እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች።
38በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።
39የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፦ “ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና፡” ብሎ በልቡ አሰበ።
40ኢየሱስም መልሶ፦ “ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ፡” አለው። እርሱም፦ “መምህር ሆይ፥ ተናገር፡” አለ።
41“ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ።
42የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?”
43ስምዖንም መልሶ፦ “ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል፡” አለ። እርሱም፦ “በእውነት ፈረድህ፡” አለው።
44ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች።
45አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም።
46አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች።
47ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።”
48እርስዋንም፦ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፡” አላት።
49ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፦ “ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?” ይሉ ጀመር።
50ሴቲቱንም፦ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።
ሉቃ 8:4-15
4ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ ከከተማዎችም ሁሉ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በምሳሌ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦
5“ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት።
6ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ።
7ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው።
8ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህን በተናገረ ጊዜ፦ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፡” ብሎ ጮኸ።
9ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ምንድር ነው?” ብለው ጠየቁት።
10እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው።”
11“ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
12በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።
13በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው።
14“በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም።
15በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”