መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕስ፡- አባይ ወደ ደም ይለወጣል

27 ቁጥሮች2አማርኛ

ዘጸ 7:14-25

14እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም ለመልቀቅ እንቢ አለ።

15ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፥ ትገናኘውም ዘንድ አንተ በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ እባብም ሆና የተለወጠችውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ።

16እንዲህም ትለዋለህ፦ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር፦ በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ፡ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤’ እነሆም እስከ ዛሬ አልሰማህም።

17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ የወንዙን ውኃ በእጄ ባለችው በትር እመታለሁ፥ ውኃውም ተለውጦ ደም ይሆናል።

18በወንዙም ያሉት ዓሦች ይሞታሉ፥ ወንዙም ይገማል፤ ግብፃውያንም የወንዙን ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ።’ ”

19እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “አሮንን፦ ‘በትርህን ውሰድ፥ ደምም እንዲሆኑ በግብፅ ውኆች በወንዞቻቸውም በመስኖቻቸውም በኩሬዎቻቸውም በውኃ ማከማቻዎቻቸውም ሁሉ ላይ እጅህን ዘርጋ፡’ በለው፤ በግብፅም አገር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል።”

20ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በባሪያዎቹም ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ።

21በወንዙም የነበሩ ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ገማ፥ ግብፃውያንም ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉም ደሙም በግብፅ አገር ሁሉ ነበረ።

22የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም።

23ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፥ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም።

24ግብፃውያንም ሁሉ የወንዙን ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉምና በወንዙ አጠገብ ውኃ ሊጠጡ ቆፈሩ።

25እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ።

ዘጸ 8:1-15

1እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ፥ እንዲህም በለው፦ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።

2ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤

3ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ባሪያዎችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ምድጆችህም፥ ወደ ቡሃቃዎችህም ይገባሉ፤

4ጓጕንቸሮችም በአንተ በሕዝብህም በባሪያዎችም ሁሉ ላይ ይወጣሉ።’ ”

5እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “አሮንን፦ ‘በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖቹ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አውጣ፡’ በለው።”

6አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፥ የግብፅንም አገር ሸፈኑ።

7ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ።

8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፦ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ፡” አላቸው።

9ሙሴም ፈርዖንን፦ “ጓጕንቸሮቹ ከአንተ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ ለባሪያዎችህም ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ አስታውቀኝ፡” አለው።

10እርሱም፦ “ነገ፡” አለ። ሙሴም፦ “አምላካችንን እግዚአብሔርን የሚመስል እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንደ ቃልህ ይሁን።

11ጓጕንቸሮቹም ከአንተ ከቤቶችህም ከባርያዎችህም ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ፡” አለ።

12ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

13እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ።

14እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች።

15ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልሰማቸውም።