የአልዓዛር ትንሣኤ

28 ቁጥሮችአማርኛ

ዮሐ 11:17-44

17ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው።

18ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች።

19ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር።

20ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር።

21ማርታም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤

22አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ” አለችው።

23ኢየሱስም፦ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት።

24ማርታም፦ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው።

25ኢየሱስም አላት፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤

26ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን?”

27እርስዋም፦ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው።

28ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ፦ “መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል” አለቻት።

29እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤

30ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር።

31ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት።

32ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፡” አለችው።

33ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ፡ በራሱም ታወከ፤

34“ወዴት አኖራችሁት?” አለም። እነርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ፡” አሉት።

35ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።

36ስለዚህ አይሁድ፦ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ” አሉ።

37ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ፦ “ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን?” አሉ።

38ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር።

39ኢየሱስ፦ “ድንጋዩን አንሡ” አለ። የሞተውም እኅት ማርታ፦ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል” አለችው።

40ኢየሱስ፦ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት።

41ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ።፦ “አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ።

42ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ።”

43ይህንም ብሎ፡ በታላቅ ድምፅ፦ “አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና፡” ብሎ ጮኸ።

44የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም፦ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት፡” አላቸው።