የቤተ መቅደሱን ማጽዳት

110 ቁጥሮች5አማርኛ

ማቴ 21:12-13

12ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና፦

13“ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት” አላቸው።

ማቴ 21:23-46

23ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና፦ “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት።

24ኢየሱስም መልሶ፦ “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤

25የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው?” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ፦ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፦ ‘እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤

26‘ከሰው’ ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን፡” አሉ።

27ለኢየሱስም መልሰው፦ “አናውቅም” አሉት። እርሱም ደግሞ፦ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

28“ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ‘ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ፡’ አለው።

29እርሱም መልሶ፦ ‘አልወድም’ አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ።

30ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው፡ እርሱም መልሶ፦ ‘እሺ ጌታዬ፡’ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም።”

31“ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው?” “ፊተኛው” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።

32ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።”

33“ሌላ ምሳሌ ስሙ፦ የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።

34የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ።

35ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት።

36ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው።

37በኋላ ግን፦ ‘ልጄንስ ያፍሩታል’ ብሎ ልጁን ላከባቸው።

38“ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፦ ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ፡’ ተባባሉ።

39ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት።

40እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?”

41እነርሱም፦ “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል” አሉት።

42ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው፡’ የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን?

43ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።

44በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።”

45የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤

46ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።

ማቴ 22:1-46

1ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ፦

2“መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች።

3የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም።

4ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ፦ ‘የታደሙትን፦ እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ፥’ በሉአቸው፡ አለ።

5“እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤

6የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው፡ ገደሉአቸውም።

7ንጉሡም ተቈጣ፥ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።

8“በዚያን ጊዜ ባሮቹን፦ ‘ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤

9እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ፡’ አለ።

10“እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት።

11ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና፦

12‘ወዳጄ ሆይ፥ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ አለው እርሱም ዝም አለ።

13በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን፦ ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አለ።

14የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

15ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ።

16ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እነርሱም፦ “መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤

17እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” አሉት።

18ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ፦ “እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ?

19የግብሩን ብር አሳዩኝ፡” አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት።

20እርሱም፦ “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” አላቸው።

21“የቄሣር ነው” አሉት። በዚያን ጊዜ፦ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” አላቸው።

22ይህንም ሰምተው ተደነቁ፥ ትተውትም ሄዱ።

23በዚያን ቀን፦ “ትንሣኤ ሙታን የለም” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥

24እንዲህም ብለው ጠየቁት፦ “መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ፡ አለ።

25ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤

26እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ።

27ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች።

28ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?”

29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።

30በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም።

33ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ።

34ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ።

35ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው፦

36“መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ብሎ ጠየቀው።

37ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።

38ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

39ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ፡ የምትለው ናት።

40በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።”

45ዳዊትስ፦ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል?” አላቸው።

46አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።

ማቴ 23:1-39

1በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦

2“ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።

3ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።

4ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።

5ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥

6በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥

7በገበያም ሰላምታና፦ ‘መምህር ሆይ፡ መምህር ሆይ፡’ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።

8እናንተ ግን፦ ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ።

9አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ።

10ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፦ ‘ሊቃውንት’ ተብላችሁ አትጠሩ።

11ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል።

12ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።”

13“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።

14እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ።

15እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።

16እናንተ፦ ‘ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል’ የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ።

17እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ?

18“ደግማችሁም፦ ‘ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል’ ትላላችሁ።

19እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው?

20“እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤

21በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤

22በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።

23“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።

24እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ።

25“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ።

26አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ።

27እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።

28“እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል።

29እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና፦

30‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር’ ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።

31“እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።

32እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ።

33“እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?

34ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤

35“ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።

36እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።”

37ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።

38እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።

39እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።

ማቴ 21:28-32

28“ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ‘ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ፡’ አለው።

29እርሱም መልሶ፦ ‘አልወድም’ አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ።

30ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው፡ እርሱም መልሶ፦ ‘እሺ ጌታዬ፡’ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም።”

31“ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው?” “ፊተኛው” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።

32ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።”