የበኣል ነቢያት
24 ቁጥሮችአማርኛ1ኛ ነገ 18:17-40
17አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ፦ እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው።
18ኤልያስም፦ እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም።
19አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ፡ አለ።
20አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።
21ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ፦ እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፡ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም።
22ኤልያስም ሕዝቡን አለ፦ ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው።
23ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፥ እየብልቱም ይቍረጡት፥ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፥ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፥ በበታቹም እሳት አልጨምርም።
24እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን። ሕዝቡም ሁሉ፦ ይህ ነገር መልካም ነው፡ ብለው መለሱ።
25ኤልያስም የበኣልን ነቢያት፦ እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፥ በበታቹም እሳት አትጨምሩ፡ አላቸው።
26ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ፦ በኣል ሆይ፥ ስማን፡ እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር።
27በቀትርም ጊዜ ኤልያስ፦ አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፥ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፥ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል፡ እያለ አላገጠባቸው።
28በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር።
29ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም።
30ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ፦ ወደ እኔ ቅረቡ፥ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ።
31ኤልያስም፦ ስምህ እስራኤል ይሆናል፡ የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ።
32ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚይዝ ጕድጓድ ቈፈረ።
33እንጨቱንም በተርታ አደረገ፥ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቈረጠ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረና፦
34አራት ጋን ውኃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ፡ አለ። ደግሞም፦ ድገሙ፡ አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም፦ ሦስተኛ አድርጉ፡ አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ።
35ውኃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን በውኃ ሞላው።
36መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ፦ አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ።
37አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፡ አለ።
38የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች።
39ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው፦ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው፡ አሉ።
40ኤልያስም፦ ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ፡ አላቸው። ያዙአቸውም፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ ወስዶ በዚያ አሳረዳቸው።