አሥርቱ ትእዛዛት።
17 ቁጥሮችአማርኛዘጸ 20:1-17
1እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦
2“ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ።
3“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።
4“በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ።
5አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤
6ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።
7“የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።
8“የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።
9ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤
10ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤
11እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።
12“አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።
13“አትግደል።
14“አታመንዝር።
15“አትስረቅ።
16“በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
17“የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።”