አንበጣዎች
17 ቁጥሮች2አማርኛዘጸ 10:12-20
12እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “በግብፅ አገር ላይ እንዲወጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ ስለ አንበጣዎች በግብፅ አገር ላይ እጅህን ዘርጋ፡” አለው።
13ሙሴም በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ እግዚአብሔርም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ ማለዳም በሆነ ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ።
14አንበጣዎችም በግብፅ አገር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፤ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደ ፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም።
15የምድሩንም ፊት ፈጽመው ሸፈኑት አገሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር ዛፍም የምድር ሣርም በግብፅ አገር ሁሉ አልቀረም።
16ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት ጠራ፦ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን እናንተንም በደልሁ፤
17አሁን እንግዲህ በዚህ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፥ ይህንም ሞት ብቻ ከእኔ ያነሣልኝ ዘንድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑ፡” አላቸው።
18ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመነ።
19እግዚአብሔርም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን አስወገደ፥ አንበጣዎችንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ አንበጣም በግብፅ ዳርቻ ሁሉ አልቀረም።
20እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም።
ዘጸ 10:21-28
21እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ሰው የሚዳስሰው ፅኑ ጨለማ ይሁን፡” አለው።
22ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ፅኑ ጨለማ ሦስት ቀን ሆነ፤
23ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ከስፍራው ማንም አልተነሣም፤ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው።
24ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ፦ “ሂዱ፥ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁ ደግሞ ከእናንተ ጋር ይሂዱ፡” አለው።
25ሙሴም፦ “አንተ ደግሞ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ትሰጠናለህ።
26አምላካችንን እግዚአብሔርን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ፥ አንድ ሰኮናም አይቀርም፤ አምላካችን የምናገለግለው ምን እንደሆነ ከዚያ እስክንደርስ አናውቅም፡” አለ።
27እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ ሊለቅቃቸውም አልወደደም።
28ፈርዖንም፦ “ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ ተጠንቀቅ፡” አለው።