የከብት በሽታ

26 ቁጥሮች3አማርኛ

ዘጸ 9:1-7

1እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው፦ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።

2ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል፡ ብትይዛቸውም፥

3እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል።

4እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም።’ ”

5እግዚአብሔርም፦ “ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል፡” ብሎ ጊዜን ወሰነ።

6እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም።

7ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።

ዘጸ 9:8-12

8እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን፦ “እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው።

9እርሱም በግብፅ አገር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብፅም አገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻህኝ የሚያመጣ ቍስል ይሆናል፡” አላቸው።

10ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ።

11ጠንቋዮችም ቍስል ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ቍስል በጠንቋዮችና በግብፃያን ሁሉ ላይ ነበረና።

12እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው አልሰማቸውም።

ዘጸ 9:13-26

13እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ማልደህ ተነሣ፥ በፈርኦንም ፊት ቆመህ በለው፦ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ።

14በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎችህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ።

15አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤

16ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ።

17እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን?

18እነሆ ነገ በዚህ ጊዜ፥ ከተመሰረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ።

19በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንስሳ ሁሉ በረዶ ወርዶበት ይሞታልና አሁን እንግዲህ ላክ፥ ከብቶችህንም በሜዳም ያለህን ሁሉ አስቸኵል።’ ”

20ከፈርዖንም ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ቃል የፈራ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤

21የእግዚአብሔርንም ቃል ያላሰበ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ።

22እግዚአብሔርም ሙሴን፦ “በግብፅ አገር በሰው በእንስሳም በእርሻም ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብፅ አገር ሁሉ በረዶ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፡” አለው።

23ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ላይ በረዶ አዘነበ።

24በረዶም ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እሳት ይቃጠል ነበር፥ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ ሕዝብ ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ያልሆነ እጅግ ታላቅ ነበረ።

25በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ሰውንና እንስሳን መታ፤ በረዶውም የእርሻን ቡቃያ ሁሉ መታ፥ የአገሩንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ።

26የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም አገር ብቻ በረዶ አልወረደም።