የሮብዓም ጥበብ የጎደለው ውሳኔ

15 ቁጥሮችአማርኛ

1ኛ ነገ 12:1-15

1እስራኤል ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ።

2እንዲህም ሆነ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ፥ እርሱም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ኰብልሎ በግብፅ ተቀምጦ ነበርና፥ በግብፅም ሳለ ልከው ጠርተውት ነበርና

3ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም፦

4አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን፡ ብለው ተናገሩት።

5እርሱም፦ ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ፡ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።

6ንጉሡም ሮብዓም፦ ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።

7እነርሱም፦ ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል፡ ብለው ተናገሩት።

8እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።

9እርሱም፦ አባትህ የጫኑብንን ቀንበር አቃልልልን፡ ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው።

10ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች፦ አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን፡ ለሚሉህ ሕዝብ፦ ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች።

11አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፥ በላቸው፡ ብለው ተናገሩት።

12ንጉሡም፦ በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ፡ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።

13ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው።

14እንደ ብላቴኖችም ምክር፦ አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፡ ብሎ ተናገራቸው።

15እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተመድቦ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።