ጽድቅ

24 ቁጥሮች14አማርኛ

ዘዳ 6:25

25እርሱም እንዳዘዘን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እናደርጋት ዘንድ ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብንጠብቅ ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።

ኢዮ 29:14

14ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፤ ፍርዴም እንደ መጐናጸፊያና እንደ ኵፋር ነበረ።

ኢዮ 33:26

26ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እርሱም ሞገስን ይሰጠዋል፡ ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፤ ለሰውም ጽድቁን ይመልስለታል።

ዳዊ 1:3

3እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።

ዳዊ 15:1-5

1አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?

2በቅንነት የሚሄድ፥ ጽድቅንም የሚያደርግ፥ በልቡም እውነትን የሚናገር።

3በአንደበቱ የማይሸነግል፥ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፥ ዘመዶቹንም የማይሰድብ።

4ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፥ ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም።

5ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘላለም አይታወክም።

ዳዊ 24:3-5

3ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል?

4እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ።

5እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን፡ ከመድኃኒቱ አምላክም ምሕረትን ይቀበላል።

ዳዊ 101:3-4

3በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም፤ ሕግ ተላላፊዎችን ጠላሁ።

4ጠማማ ልብም አልተጠጋኝም፤ ክፉ ከእኔ በራቀ ጊዜ አላወቅሁም።

ምሳ 10:2

2በኃጢአት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል።

ምሳ 11:5-6

5የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፤ ኃጥእ ግን በኃጢአቱ ይወድቃል።

6ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፤ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ።

ምሳ 11:19

19በጽድቅ የሚጸና በሕይወት ይኖራል፤ ክፋትን የሚከተል ግን ለሞቱ ነው።

ምሳ 11:30

30የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚሰበስብ እርሱ ጠቢብ ነው።

ምሳ 29:7

7ጻድቅ የድሆችን ፍርድ ይመለከታል፤ ኀጥእ ግን እውቀትን አያስተውልም።

ኢሳ 33:15-17

15በጽድቅ የሚሄድ ቅን ነገርንም የሚናገር፥ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍን የሚንቅ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚያደነቍር፥ ክፋትንም ከማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን ነው።

16እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።

17ዓይኖችህ ንጉሥን በውበቱ ያዩታል፤ እነርሱም በሩቅ ያለች ምድርን ያዩአታል።

ማቴ 12:35

35መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።