የማቴዎስ ወንጌል 12

AMHEVGአማርኛ48 ጥቅሶች7:09 አዳምጥ
አዳምጥ 7:09 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር።

2ፈሪሳውያንም አይተው፦ “እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ፡” አሉት።

3እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን?

5ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን?

6ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።

7ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር።

8የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”

9ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ።

10እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ፦ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት።

11እርሱ ግን፦ “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?

12እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል፡” አላቸው።

13ከዚያም በኋላ ሰውየውን፦ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች።

14ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።

15ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤

16በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦

18“እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል።

19አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም።

20ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም።

21አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

22ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው።

23ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና፦ “እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።

24ፈሪሳውያን ግን ሰምተው፦ “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም፡” አሉ።

25ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም።

26ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?

27እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።

28“እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።

29ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።

30ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል።

31“ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም።

32በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።”

33“ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ።

34እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና።

35መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።

36እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤

37ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ።”

38በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፦ “መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን፡” አሉ።

39እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።

40ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።

41የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።

42ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።”

43“ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም።

44በዚያን ጊዜም፦ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል።

45ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።”

46ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።

47አንዱም፦ “እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።

48እርሱ ግን ለነገረው መልሶ፦ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው።

49እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ እንዲህ አለ፦ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤

50በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና።”

ማብራሪያ

12:1-8 በእርሻ ማሳዎች ውስጥ ሳሉ፣ ደቀ መዛሙርቱ እሸት መቁረጥ ጀመሩ። የእግዚአብሔር ሕግም ይህን ይፈቅድ ነበር (ዘዳግም 23:25)። ይህ ለክርስቶስና ለደቀ መዛሙርቱ እምብዛም የምግብ ስንቅ ቢሆንም፣ በእርሱ ረክተው ነበር። ፈሪሳውያን የሌላ ሰው እሸት ስለወሰዱ አልነበረም የነቀፏቸው፤ ይልቁንም በሰንበት ቀን ስላደረጉት ነበር። ክርስቶስ የመጣው ተከታዮቹን ከፈሪሳውያን የተዛቡ ልማዶቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ከሆኑት ሕግጋቶቻቸውም ጭምር ነጻ ሊያወጣ ነው። እርሱም ያደረጉትን ነገር አጸደቀላቸው። ታላላቆቹ ምኞቶቻቸው እንዲፈጸሙ አይፈቀድላቸውም፤ ትንሾቹ ግን ፍላጎቶቻቸው ይስተዋላሉ። አስፈላጊ የሆኑት ሥራዎች በሰንበት ቀን ይፈቀዳሉ፤ የሰንበት ዕረፍትም የሰንበትን አምልኮ ለማራመድ እንጂ ለማደናቀፍ አይደለም። ለጤናና ለምግብ የሚያስፈልገው ዝግጅት መደረግ አለበት፤ ነገር ግን አገልጋዮች በቤት ውስጥ ተይዘው፣ ቤተሰቦችም በጌታ ቀን ለጎብኚዎች ድግስ ለማዘጋጀት ወይም ለቅምጥልነት ሲሉ በችኮላና በግርግር ውስጥ ሲሆኑ፣ ጉዳዩ እጅግ የተለየ ነው። እንደነዚህ ያሉት ነገሮች እንዲሁም በክርስቲያኖች ዘንድ የተለመዱ ሌሎች ብዙ ነገሮችም የሚወቀሱ ናቸው። በሰንበት ማረፍ ለሰው ጥቅም ታዝዞ ነበር (ዘዳግም 5:14)። ምንም ሕግ የራሱን ዓላማ በሚጻረር መልኩ ሊተረጎም አይገባም። ክርስቶስ የሰንበት ጌታ እንደመሆኑ መጠን፣ ቀኑም ሥራውም ለእርሱ የተወሰነ መሆን አለበት።

፲፪:፱-፲፫ ክርስቶስ የምሕረት ሥራዎች በጌታ ቀን ሊሠሩ ሕጋዊና የተገቡ መሆናቸውን ያሳያል። በሰንበት ቀናት መልካም ለማድረግ ከአምልኮ ተግባራት ይልቅ ብዙ መንገዶች አሉ። በሽተኞችን መጠየቅ፣ ድሆችን መርዳት፣ ፈጣን እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማገዝ፣ ወጣቶችን ለነፍሳቸው እንዲጨነቁ ማስተማር፤ እነዚህ መልካም ሥራዎች ናቸው። እነዚህም ከፍቅርና ከበጎነት የተነሣ፣ በትሕትናና ራስን በመካድ መደረግ አለባቸው፣ ተቀባይነትም ያገኛሉ (ዘፍ ፬:፯)። ይህ፣ ክርስቶስ እንደሠራቸው ሌሎች ፈውሶች ሁሉ፣ መንፈሳዊ ትርጉም ነበረው። በተፈጥሮአችን እጆቻችን የደረቁ ናቸው፣ በራሳችንም ምንም መልካም ነገር ለማድረግ አንችልም። ክርስቶስ ብቻ በጸጋው ኃይል ይፈውሰናል። ለሞተው ነፍስ ሕይወትን በመስጠት የደረቀውን እጅ ይፈውሳል፤ በእኛም ፈቃድንና መሥራትን ይሠራልና። በትእዛዙም ከቃሉ የተሰጠ የጸጋ ተስፋ አለና።

፲፪፥፲፬-፳፩ ፈሪሳውያን ኢየሱስ ለሞት እንዲፈረድበት የሚከስሱበትን ምክንያት ለማግኘት ተማከሩ። የእነርሱን ዕቅድ ስለሚያውቅ፥ ጊዜውም ገና ስላልደረሰለት፥ ከዚያ ስፍራ ተለየ። በውኃ ውስጥ ፊት ለፊት በትክክል እንደሚዛመድ ሁሉ፥ በነቢዩ የተገለጸው የክርስቶስ ባሕርይ ከወንጌላውያን በተገለጸው ጠባዩና አኗኗሩ ጋር ከዚያም በላይ በትክክል ይዛመዳል። ነፍሳችንን እንደዚህ ደግና ታማኝ ለሆነ ወዳጅ በደስተኛ እምነት አደራ እንስጥ። ከመስበር ይልቅ፥ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ ያጠነክራል። የሚጤሰውን ገመድ ከማጥፋት ይልቅ፥ ይልቁንም ወደ ነበልባል ያነድደዋል። አከራካሪና ቁጡ ክርክሮችን እናቁም፤ ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን እርስ በእርሳችን እንቀበል ። በጌታችን የጸጋ ደግነት እየተበረታታን ሳለ፥ መንፈሱ በእኛ ላይ እንዲያርፍ፥ ምሳሌውንም እንድንመስል እንዲያደርገን መጸለይ ይገባናል።

12:22-30 በሰይጣን ሥልጣን ሥር ያለችና በእርሱ ምርኮኛ የሆነች ነፍስ በእግዚአብሔር ነገሮች ዕውር ናት፤ በጸጋው ዙፋንም ላይ ዲዳ ናት፤ ምንም አታይም፤ ዓላማ ያለውም ነገር አትናገርም። ሰይጣን ባለማመን ዓይኖችን ያሳውራል፤ ከጸሎትም ከንፈሮችን ይዘጋል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6