ፋሲካ

59 ቁጥሮች6አማርኛ

ዘጸ 12:3-49

3ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም፦ ‘በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ።

4የቤቱ ሰዎች ቍጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደ ነፍሶቻቸው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ።

5የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ።

6በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት።

7ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቅቡት።

8በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል።’

9ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት።

10ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት።

11ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ትበሉታላችህ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።

12“እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

13ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም።

14“ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ።

15ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ።

16በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ከሚበላው በቀር በእነርሱም ምንም አትሠሩም፥ ይህንም ብቻ ታደርጉታላችሁ።

17“በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ አገር አውጥቼአለሁና የቂጣውንም በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ።

18በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ከወሩም እስከ ሀያ አንድ ቀን በመሸ ጊዜ የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።

19ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ።

20እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ።”

21ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ አላቸው፦ “በየቤታችሁ ጠቦት ምረጡ፥ ወስዳችሁም ለፋሲካ እረዱት።

22ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለውም ደም ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ፤ ከእናንተም አንድ ሰው ከቤቱ ደጅ እስኪነጋ ድረስ አይውጣ።

23እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም።

24ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ሥርዓት አድርጋችሁ ይህችን ነገር ጠብቁ።

25እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት።

26እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ፦ ‘ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድር ነው?’ ባሉአችሁ ጊዜ፥

27እናንተ፦ ‘በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት፡’ ትሉአቸዋላችሁ።” ሕዝቡም ተጎነበሰ ሰገደም።

28የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ።

29እንዲህም ሆነ፤ እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞቹ በኵር ድረስ፥ የግብፃውያንን በግብፅ ምድር የተገኘውን በኵር ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵሮች ሁሉ መታ።

30ፈርዖንም ባሪያዎቹም ሁሉ ግብፃውያንም ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብፅ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ።

31ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ፦ “እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፥ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አገልግሉ፤

32እንዳላችሁም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ፡” አለ።

33ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ ሕዝቡን ያስቸኵሉአቸው ነበር፦ “ሁላችን እንሞታለን፡” ብለዋልና።

34ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ቡሃቃውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት።

35የእስራኤልም ልጆች ሙሴ እንዳዘዘ አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ።

36እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙ።

37የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ።

38ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ።

39ከግብፅም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ጋገሩ፥ አልቦካም ነበርና ቂጣ እንጎቻ አደረጉት፤ ግብፃውያን በመውጣት ስላስቸኰሉአቸው ይቈዩ ዘንድ አልተቻላቸውም፥ ስንቅም አላሰናዱም ነበር።

40የእስራኤልም ልጆች በግብፅ ምድር የተቀመጡት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነው።

41እንዲህም ሆነ፤ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ ከግብፅ ምድር ወጣ።

42ይህች ሌሊት ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ እስከ ልጅ ልጃቸው ድረስ ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት።

43እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን አለ፦ “ይህ የፋሲካ ሕግ ነው፤ ከእርሱ እንግዳ ሰው አይብላ።

44በብር የተገዛ ባሪያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ።

45መጻተኛና ሞያተኛ ግን ከእርሱ አይብሉ።

46በአንድ ቤትም ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንትም አትስበሩበት።

47የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ያድርጉት።

48እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድድ፥ አስቀድሞ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ።

49ለአገር ልጅ በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ እንግዶች አንድ ሥርዓት ይሆናል።”

ዘጸ 13:3

3ሙሴም ሕዝቡን አለ፦ “ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጣችሁበትን ይህን ቀን አስቡ፥ እግዚአብሔር ከዚህ ቦታ በብርቱ እጅ አውጥቶአችኋልና፤ ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ።

ዘጸ 13:6

6ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር በዓል ይሆናል።

ዘጸ 23:15-18

15የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በአቢብ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ።

16በእርሻም የምትዘራትን የፍሬህን በኵራት የመከር በዓል፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ ባከማቸህ ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ።

17በዓመት ሦስት ጊዜ በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ።

18የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስኪነጋ አይደር።

ዘጸ 34:18

18የቂጣውን በዓል ትጠብቀዋለህ። በአቢብ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና በታዘዘው ዘመን በአቢብ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ።

ዘሌ 23:4-8

4“ ‘እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሰ ጉባኤ ናቸው።

5በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።

6በዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብሉ።

7በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

8ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።’ ”