የፈርዖን ህልሞች

36 ቁጥሮችአማርኛ

ዘፍ 41:1-36

1ከሁለት ዓመት በኋላም ፈርዖን ሕልምን አየ፥ እነሆም፥ በወንዙ ዳር ቆሞ ነበር።

2እነሆም፥ መልካቸው ያማረ ሥጋቸውም የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፥ በውኃውም ዳር በመስኩ ይሰማሩ ነበር።

3ከእነርሱም በኋላ እነሆ መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዝ ወጡ፥ በእነዚያም ላሞች አጠገብ በወንዙ ዳር ይቆሙ ነበር።

4መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ እነዚያም ላሞች መልካቸው ያማረውን ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ።

5ደግሞም ተኛ ሁለተኛም ሕልምን አየ። እነሆም በአንድ አገዳ ላይ የነበሩ ያማሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች ወጡ፤

6እነሆም ከእነርሱ በኋላ የሰለቱና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤

7የሰለቱትም እሸቶች ሰባቱን ያማሩና የዳበሩ እሸቶች ዋጡአቸው።

8ፈርዖንም ነቃ፥ እነሆም ሕልም ነበረ። በነጋም ጊዜ ነፍሱ ታወከችበት፤ ወደ ሕልም ተርጓሚዎች ሁሉ ወደ ግብፅ ጠቢባንም ሁሉ ልኮ ወደ እርሱ ጠራቸው፤ ፈርዖንም ሕልሙን ነገራቸው፥ ነገር ግን ከእነርሱ ለፈርዖን የሚተረጕም አልተገኘም።

9የዚያን ጊዜ የጠጅ አሳላፈዎቹ አለቃ እንዲህ ብሎ ለፈርዖን ተናገረ፦ “እኔ ኃጢአቴን ዛሬ አስባለሁ፤

10ፈርዖን በባሪይዎቹ ላይ ተቆጣ፥ እኔንም የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ በግዞት ስፍራ በዘበኞች አለቃ ቤት አኖረን፤

11እኛም በአንዲት ሌሊት ሕልምን አለምን፥ እኔና እርሱ፤ እያንዳንዳችን እንደ ሕልማችን ትርጓሜ አለምን።

12በዚያም የዘበኞቹ አለቃ ባሪያ የሆነ አንድ ዕብራዊ ጕልማሳ ከእኛ ጋር ነበረ፤ ለእርሱም ነገርነው፥ ሕልማችንንም ተረጐመልን፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሕልሙ ተረጐመልን።

13እንዲህም ሆነ፤ እንደ ተረጐመልን እንደዚያው ሆነ፤ እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስሁ፥ እርሱም ተሰቀለ።”

14ፈርዖንም ልኮ ዮሴፍን አስጠራ፥ ከግዞት ቤትም አስቸኰሉት፤ እርሱም ተላጨ፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ ፈርዖንም ገባ።

15ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ “ሕልምን አየሁ፥ የሚተረጕመውም አልተገኘም፤ ሕልምን እንደ ሰማህ፥ እንደ ተረጐምህም ስለ አንተ ሰማሁ።”

16ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “ይህ በእኔ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን ለፈርዖን በደኅንነት ይመልስለታል።”

17ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤

18እነሆም፥ ሥጋቸው የወፈረ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ፥ በመስኩም ይሰማሩ ነበር፤

19ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደከሙ መልካቸውም እጅግ የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ እንደ እነርሱ መልከ ክፉ ከቶ አላየሁም፤

20የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ወፍራሞቹን ሰባት ላሞች ዋጡአቸው፥

21በሆዳቸውም ተዋጡ፤ በሆዳቸውም እንደተዋጡ አልታወቀም፥ መልካቸውም በመጀመሪያ እንደ ነበረው የከፋ ነበረ። ነቃሁም።

22“በሕልሜም እነሆ የዳበሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች በአንድ አገዳ ሲወጡ አየሁ፤

23ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደረቁና የሰለቱ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤

24የሰለቱት እሸቶች ያማሩትን ሰባቱን እሸቶች ዋጡአቸው። ለሕልም ተርጓሚዎችም ሕልሜን ነገርሁ የሚተረጕምልኝም አጣሁ።”

25ዮሴፍም ፈርዖንን አለው፦ “የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን ነግሮታል።

26ሰባቱ መልካካሞች ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም መልካካሞች እሸቶች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙ አንድ ነው።

27ከእነርሱም በኋላ የወጡት የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ የሰለቱትና የምሥራቅ ነፋስ የመታቸው ሰባቱም እሸቶች እነርሱ ራብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ናቸው።

28ለፈርዖን የነገርሁት ነገር ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው።

29እነሆ በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ፤

30ደግሞ ከዚህ በኋላ የሰባት ዓመት ራብ ይመጣል፥ በግብፅ አገር የነበረውም ጥጋብ ሁሉ ይረሳል፤ ራብም ምድርን በጣም ያጠፋል፤

31በኋላ ከሚሆነው ከዚያ ራብ የተነሣም በምድር የሆነው ጥጋብ አይታወቅም፥ እጅግ ጽኑ ይሆናልና።

32ሕልሙም ለፈርዖን ደጋግሞ መታየቱ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ያደርገዋል።

33አሁንም ፈርዖን ብልህና አዋቂ ሰውን ይፈልግ፥ በግብፅ ምድር ላይም ይሹመው።

34ፈርዖን በምድር ላይ ሹማምትን ይሹም፤ በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ፍሬ በግብፅ ምድር ሁሉ ከአምስት እጅ አንደኛውን ይውሰድ።

35የሚመጡትን የመልካሞቹን ዓመታት እህላቸውን ያከማቹ፤ ስንዴውንም ከፈርዖን እጅ በታች ያኑሩ፥ እህሎችም በከተሞች ይጠበቁ።

36በግብፅ ምድር ስለሚሆነው ስለ ሰባቱ ዓመታት ራብ እህሉ ተጠብቆ ይኑር፥ ምድሪቱም በራብ አትጠፋም።”