የኢየሱስ የሕጉ ማጠቃለያ
11 ቁጥሮች2አማርኛማር 12:28-34
28ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፦ “ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት?” ብሎ ጠየቀው።
29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ ‘እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥
30አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፡’ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።
31ሁለተኛይቱም፦ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡’ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።”
32ጻፊውም፦ “መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤
33በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ፡ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው፡” አለው።
34ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ፦ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።