የአጋር ታሪክ - 2
13 ቁጥሮችአማርኛዘፍ 21:9-21
9ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው።
10አብርሃምንም፦ “ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ፤ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና፡” አለችው።
11ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት።
12እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፤ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና።
13የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና።”
14አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፤ እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች።
15ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው፤
16እርስዋም ሄደች፦ “ብላቴናው ሲሞት አልየው፡” ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች።
17እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፦ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ።
18ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።”
19እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።
20እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፤ አደገም፥ በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ።
21በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት።