1አንቺ የመኰንን ልጅ ሆይ፥ እግሮችሽ በጫማ ውስጥ እንዴት ውቦች ናቸው! ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ፡ እንደ ዕንቍዎች ይመስላሉ።
2እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፤ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው።
3ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ፡ እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው።
4አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፤ ዓይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ፡ እንደ ውኃ ኵሬዎች ናቸው፤ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አፋዛዥ እንደሚመለከት፡ እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው።
5ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፤ የራስሽም ጠጕር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፤ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል።
6ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ!
7ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ።
8ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ፡ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ፡ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው።
9ጕሮሮሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው።
10እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው።
11ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር።
12ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፤ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ፡ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያ ውዴን እሰጥሃለሁ።
13ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፤ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፤ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።