1አንቺ የልዑል ልጅ ሆይ፤ ነጠላ ጫማ የተጫሙ እግሮችሽ እንዴት ያምራሉ ሞገስን የተጐናጸፉ ዳሌዎችሽ፣ ብልኅ አንጥረኛ የተጠበባቸውን የዕንቊ ሐብል ይመስላሉ።
2ዕንብርትሽ ጥሩ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት፣ እንደ ክብ ጽዋ ነው፤ ወገብሽ ዙሪያውን በውብ አበባ የታሰረ የስንዴ ክምር ይመስላል።
3ሁለት ጡቶችሽ፣ መንታ የዋልያ ግልገሎችን ይመስላሉ።
4ዐንገትሽ በዝሆን ጥርስ እንዳጌጠ መጠበቂያ ማማ ነው፤ ዐይኖችሽ በባትረቢ በር አጠገብ እንዳሉት፣ እንደ ሐሴቦን ኵሬዎች ናቸው፤ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አቅጣጫ እንደሚመለከት፣ እንደ ሊባኖስ መጠበቂያ ማማ ነው።
5የራስሽ ቅርጽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ አክሊል ሆኖልሻል፤ ጠጒርሽ የሐር ጒንጒን የመሰለ ነው፤ ንጉሡም በሹሩባሽ ታስሮ ተይዞአል።
6እንዴት ውብ ነሽ! እንዴትስ ደስ የምትይ ነሽ! ፍቅሬ ሆይ፤ የምታስደስቺ ነሽ።
7ቁመናሽ እንደ ዘንባባ ዛፍ መለል ያለ ነው፤ ጡቶችሽም የፍሬውን ዘለላ ይመስላሉ።
8እኔም፣ “የዘንባባውን ዛፍ እወጣለሁ፤ ዘለላዎቹንም እይዛለሁ” አልሁ። ጡቶችሽ የወይን ዘለላ፣ የእስትንፋስሽም መዐዛ እንደ እንኰይ ፍሬ ይሁኑ፤
9ከናፍሮችሽም እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ይጣፍጡ። የወይን ጠጁ በቀስታ እየተንቈረቈረ፣ ወደ ውዴ ከንፈሮችና ጥርሶች ይውረድ።
10እኔ የውዴ ነኝ፤ የእርሱም ምኞት እኔው ነኝ።
11ውዴ ሆይ፤ ና ወደ ገጠር እንሂድ፤ ወደ መንደርም ገብተን እንደር፤
12ማልደን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ እንሂድ፣ ወይኑ እንቡጥ አውጥቶ፣ አበባው ፈክቶ፣ ሮማኑ አፍርቶ እንደሆነ እንይ፤ በዚያም ራሴን በፍቅር እሰጥሃለሁ።
13ትርንጐዎች መዐዛቸውን ሰጡ፤ አዲስ የተቀጠፈውም ሆነ የበሰለው፣ ጣፋጩ ፍሬ ሁሉ በደጃፋችን አለ፤ ውዴ ሆይ፤ ለአንተ አስቀምጬልሃለሁ።