የማቴዎስ ወንጌል 12

AMHNIVአማርኛ50 ጥቅሶች7:21 አዳምጥ
አዳምጥ 7:21 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር።

2ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን መደረግ የሌለበትን እያደረጉ ነው” አሉት።

3እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን?

4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገባ፤ ለካህናት እንጂ ለእርሱም ሆነ አብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ ኅብስት በላ።

5ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም?

6ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ።

7‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር።

8የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”

9ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤

10በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዶአል?” ብለው ጠየቁት።

11እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጎትቶ አያወጣውምን?

12ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል” አላቸው።

13ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላኛውም እጁ ደህና ሆነለት።

14ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ።

15ኢየሱስ ሐሳባቸውን አውቆ ከዚያ ዘወር አለ። ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤

16ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።

17ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤

18“እነሆ የመረጥሁት፣ የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል።

19አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም።

20ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም።

21አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

22ከዚህ በኋላ በጋኔን የተያዘ ዕውርና ድዳ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም ፈወሰው፤ ሰውየውም ማየትና መናገር ቻለ።

23ሕዝቡም ሁሉ ተደንቀው፣ “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።

24ነገር ግን ፈሪሳውያን ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “ይህ ሰው አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ብቻ መሆን አለበት” አሉ።

25ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በእርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ ይወድቃል፤ እርስ በእርሱም የተከፋፈለ ከተማ ወይም ቤት አይጸናም።

26ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ፣ እርስ በእርሱ ተለያይቷል ማለት ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል?

27እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በምን ሊያስወጧቸው ነው? ስለዚህ ልጆቻችሁ ይፈርዱባችኋል።

28እኔ ግን አጋንንትን የማስወጣው በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥታለች።

29“ወይስ አንድ ሰው ወደ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ ንብረቱን ለመዝረፍ ቢፈልግ፣ አስቀድሞ ያንን ኀይለኛ ሰው ሳያስር እንዴት አድርጎ ይሳካለታል? ኋላም ቤቱን መበዝበዝ ይችላል።

30“ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ሁሉ ይበትናል።

31ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም።

32ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም።

33“ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ፣ መልካም ፍሬ እንድታገኙ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ መጥፎ ዛፍ ቢኖራችሁ ግን መጥፎ ፍሬ ታገኛላችሁ።

34እናንት የእፉኝት ልጆች፤ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋልና።

35መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር በጎ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር መጥፎ ነገር ያወጣል።

36ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል።

37ምክንያቱም ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃልና።”

38ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት።

39እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።

40ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል።

41የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

42በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።

43“ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም።

44ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል።

45ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”

46ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።

47አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።

48ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት።

49በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤

50በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።”

ማብራሪያ

12:1-8 በእርሻ ማሳዎች ውስጥ ሳሉ፣ ደቀ መዛሙርቱ እሸት መቁረጥ ጀመሩ። የእግዚአብሔር ሕግም ይህን ይፈቅድ ነበር (ዘዳግም 23:25)። ይህ ለክርስቶስና ለደቀ መዛሙርቱ እምብዛም የምግብ ስንቅ ቢሆንም፣ በእርሱ ረክተው ነበር። ፈሪሳውያን የሌላ ሰው እሸት ስለወሰዱ አልነበረም የነቀፏቸው፤ ይልቁንም በሰንበት ቀን ስላደረጉት ነበር። ክርስቶስ የመጣው ተከታዮቹን ከፈሪሳውያን የተዛቡ ልማዶቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ከሆኑት ሕግጋቶቻቸውም ጭምር ነጻ ሊያወጣ ነው። እርሱም ያደረጉትን ነገር አጸደቀላቸው። ታላላቆቹ ምኞቶቻቸው እንዲፈጸሙ አይፈቀድላቸውም፤ ትንሾቹ ግን ፍላጎቶቻቸው ይስተዋላሉ። አስፈላጊ የሆኑት ሥራዎች በሰንበት ቀን ይፈቀዳሉ፤ የሰንበት ዕረፍትም የሰንበትን አምልኮ ለማራመድ እንጂ ለማደናቀፍ አይደለም። ለጤናና ለምግብ የሚያስፈልገው ዝግጅት መደረግ አለበት፤ ነገር ግን አገልጋዮች በቤት ውስጥ ተይዘው፣ ቤተሰቦችም በጌታ ቀን ለጎብኚዎች ድግስ ለማዘጋጀት ወይም ለቅምጥልነት ሲሉ በችኮላና በግርግር ውስጥ ሲሆኑ፣ ጉዳዩ እጅግ የተለየ ነው። እንደነዚህ ያሉት ነገሮች እንዲሁም በክርስቲያኖች ዘንድ የተለመዱ ሌሎች ብዙ ነገሮችም የሚወቀሱ ናቸው። በሰንበት ማረፍ ለሰው ጥቅም ታዝዞ ነበር (ዘዳግም 5:14)። ምንም ሕግ የራሱን ዓላማ በሚጻረር መልኩ ሊተረጎም አይገባም። ክርስቶስ የሰንበት ጌታ እንደመሆኑ መጠን፣ ቀኑም ሥራውም ለእርሱ የተወሰነ መሆን አለበት።

፲፪:፱-፲፫ ክርስቶስ የምሕረት ሥራዎች በጌታ ቀን ሊሠሩ ሕጋዊና የተገቡ መሆናቸውን ያሳያል። በሰንበት ቀናት መልካም ለማድረግ ከአምልኮ ተግባራት ይልቅ ብዙ መንገዶች አሉ። በሽተኞችን መጠየቅ፣ ድሆችን መርዳት፣ ፈጣን እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማገዝ፣ ወጣቶችን ለነፍሳቸው እንዲጨነቁ ማስተማር፤ እነዚህ መልካም ሥራዎች ናቸው። እነዚህም ከፍቅርና ከበጎነት የተነሣ፣ በትሕትናና ራስን በመካድ መደረግ አለባቸው፣ ተቀባይነትም ያገኛሉ (ዘፍ ፬:፯)። ይህ፣ ክርስቶስ እንደሠራቸው ሌሎች ፈውሶች ሁሉ፣ መንፈሳዊ ትርጉም ነበረው። በተፈጥሮአችን እጆቻችን የደረቁ ናቸው፣ በራሳችንም ምንም መልካም ነገር ለማድረግ አንችልም። ክርስቶስ ብቻ በጸጋው ኃይል ይፈውሰናል። ለሞተው ነፍስ ሕይወትን በመስጠት የደረቀውን እጅ ይፈውሳል፤ በእኛም ፈቃድንና መሥራትን ይሠራልና። በትእዛዙም ከቃሉ የተሰጠ የጸጋ ተስፋ አለና።

፲፪፥፲፬-፳፩ ፈሪሳውያን ኢየሱስ ለሞት እንዲፈረድበት የሚከስሱበትን ምክንያት ለማግኘት ተማከሩ። የእነርሱን ዕቅድ ስለሚያውቅ፥ ጊዜውም ገና ስላልደረሰለት፥ ከዚያ ስፍራ ተለየ። በውኃ ውስጥ ፊት ለፊት በትክክል እንደሚዛመድ ሁሉ፥ በነቢዩ የተገለጸው የክርስቶስ ባሕርይ ከወንጌላውያን በተገለጸው ጠባዩና አኗኗሩ ጋር ከዚያም በላይ በትክክል ይዛመዳል። ነፍሳችንን እንደዚህ ደግና ታማኝ ለሆነ ወዳጅ በደስተኛ እምነት አደራ እንስጥ። ከመስበር ይልቅ፥ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ ያጠነክራል። የሚጤሰውን ገመድ ከማጥፋት ይልቅ፥ ይልቁንም ወደ ነበልባል ያነድደዋል። አከራካሪና ቁጡ ክርክሮችን እናቁም፤ ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን እርስ በእርሳችን እንቀበል ። በጌታችን የጸጋ ደግነት እየተበረታታን ሳለ፥ መንፈሱ በእኛ ላይ እንዲያርፍ፥ ምሳሌውንም እንድንመስል እንዲያደርገን መጸለይ ይገባናል።

12:22-30 በሰይጣን ሥልጣን ሥር ያለችና በእርሱ ምርኮኛ የሆነች ነፍስ በእግዚአብሔር ነገሮች ዕውር ናት፤ በጸጋው ዙፋንም ላይ ዲዳ ናት፤ ምንም አታይም፤ ዓላማ ያለውም ነገር አትናገርም። ሰይጣን ባለማመን ዓይኖችን ያሳውራል፤ ከጸሎትም ከንፈሮችን ይዘጋል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6