የሉቃስ ወንጌል 3

AMHNIVአማርኛ38 ጥቅሶች6:23 አዳምጥ
አዳምጥ 6:23 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሊሳኒዮስም የሳቢላኒስ አራተኛው ክፍል ገዥ በነበሩበት ጊዜ፣

2ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።

3እርሱም ለኀጢአት ስርየት የሚሆን የንስሓን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ መጣ፤

4ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል በጻፈው ቃል መሠረት ነበር፤ “በበረሓ እንዲህ ብሎ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጐዳናውንም አቅኑ፤

5ሸለቆው ሁሉ ይሞላል፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማው መንገድ ቀና፣ ሸካራውም ጐዳና ትክክል ይሆናል፤

6የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል።’ ”

7ዮሐንስም በእርሱ እጅ ሊጠመቁ የወጡትን ሰዎች እንዲህ ይላቸው ነበር፤ “እናንት የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ?

8እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ደግሞም በልባችሁ፣ ‘አብርሃም አባታችን አለን’ ማለትን አትጀምሩ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና።

9አሁን እንኳ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራም ዛፍ ሁሉ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል።”

10ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።

11ዮሐንስም፣ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” ብሎ መለሰላቸው።

12ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፤ እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት።

13እርሱም፣ “ከታዘዛችሁት በላይ ቀረጥ አትሰብስቡ” አላቸው።

14ወታደሮች ደግሞ፣ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የማንንም ገንዘብ በግፍ አትንጠቁ፤ ሰውንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁ ይብቃችሁ” አላቸው።

15ሕዝቡ በጒጒት እየተጠባበቁ ሳሉ፣ “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያሰላስሉ ነበር።

16ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔም የእርሱን የጫማ ማሰሪያ መፍታት የሚገባኝ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤

17ዐውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውንም ወደ ጐተራው ለመክተት መንሹ በእጁ ነው፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”

18ዮሐንስም በብዙ ሌሎች የምክር ቃላት ሕዝቡን እያስጠነቀቀ ወንጌልን ሰበከላቸው።

19ነገር ግን ዮሐንስ፣ የአራተኛውን ክፍል ገዥ ሄሮድስን የወንድሙ ሚስት በነበረችው በሄሮድያዳ ምክንያትና ስለ ሌሎች ሥራዎቹ በገሠጸው ጊዜ፣

20ሄሮድስ ይህን በሌላው ሁሉ ላይ በመጨመር፣ ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገባው።

21ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቀ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እየጸለየም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤

22መንፈስ ቅዱስም በአካላዊ ቅርጽ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ ከሰማይም፣ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ መጣ።

23ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ነበር፤ ሕዝቡም እንደ መሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፣ የኤሊ ልጅ፣

24የማቲ ልጅ፣ የሌዊ ልጅ፣ የሚልኪ ልጅ፣ የዮና ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣

25የማታትዩ ልጅ፣ የአሞጽ ልጅ፣ የናሆም ልጅ፣ የኤሲሊም ልጅ፣ የናጌ ልጅ፣

26የማአት ልጅ፣ የማታትዩ ልጅ፣ የሴሜይ ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣ የዮዳ ልጅ፣

27የዮናን ልጅ፣ የሬስ ልጅ፣ የዘሩባቤል ልጅ፣ የሰላትያል ልጅ፣ የኔሪ ልጅ፣

28የሚልኪ ልጅ፣ የሐዲ ልጅ፣ የዮሳስ ልጅ፣ የቆሳም ልጅ፣ የኤልሞዳም ልጅ፣ የኤር ልጅ፣

29የዮሴዕ ልጅ፣ የኤልዓዘር ልጅ፣ የዮራም ልጅ፣ የማጣት ልጅ፣ የሌዊ ልጅ፣

30የስምዖን ልጅ፣ የይሁዳ ልጅ፣ የዮሴፍ ልጅ፣ የዮናም ልጅ፣ የኤልያቄም ልጅ፣

31የሜልያ ልጅ፣ የማይናን ልጅ፣ የማጣት ልጅ፣ የናታን ልጅ፣ የዳዊት ልጅ፣

32የእሴይ ልጅ፣ የኢዮቤድ ልጅ፣ የቦዔዝ ልጅ፣ የሰልሞን ልጅ፣ የነአሶን ልጅ፣

33የአሚናዳብ ልጅ፣ የአራም ልጅ፣ የአሮኒ ልጅ፣ የኤስሮም ልጅ፣ የፋሬስ ልጅ፣ የይሁዳ ልጅ፣

34የያዕቆብ ልጅ፣ የይስሐቅ ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ፣ የታራ ልጅ፣ የናኮር ልጅ፣

35የሴሮህ ልጅ፣ የራጋው ልጅ፣ የፋሌቅ ልጅ፣ የአቤር ልጅ፣ የሳላ ልጅ፣

36የቃይንም ልጅ፣ የአርፋክስድ ልጅ፣ የሴም ልጅ፣ የኖኅ ልጅ፣ የላሜህ ልጅ፣

37የማቱሳላ ልጅ፣ የሄኖክ ልጅ፣ የያሬድ ልጅ፣ የመላልኤል ልጅ፣ የቃይናን ልጅ፣

38የሄኖስ ልጅ፣ የሤት ልጅ፣ የአዳም ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ።

ማብራሪያ

3:1-14 የዮሐንስ አገልግሎት ስፋትና ዓላማ ሰዎችን ከኃጢአታቸው እንዲመልስና ወደ መድኃኒታቸው እንዲያቀርብ ነበር። እርሱ የመጣው ኑፋቄን ወይም ቡድንን ሳይሆን፣ የእምነት ኑሮን ለመስበክ ነበር፤ ምልክቱም ወይም ሥርዓቱም በውኃ መታጠብ ነበር። እዚህ በተጠቀሱት ቃላት ዮሐንስ የኃጢአት ስርየትን ለማግኘት የንስሓን አስፈላጊነት ሰብኳል፤ የውኃ ጥምቀትም የእውነተኛ ንስሓ ውጤቶች የሆኑትን የልብ ውስጣዊ መንጻትና መታደስ ውጫዊ ምልክት፣ እንዲሁም የእርሱ (የንስሓ) መግለጫ መሆኑን አስረድቷል። የዮሐንስ አገልግሎት በኢሳ 40:3 ላይ የተጻፈው የቅዱሳት መጻሕፍት ትንቢት መፈጸም ነው። ከፍ ከፍ ያሉ ሐሳቦችን በማውረድ፣ ወደ ክርስቶስም መታዘዝ በማምጣት፣ ልብን በማስተካከል፣ እንዲሁም በክርስቶስና በጸጋው መንገድ ላይ የሚገታንን ነገር ሁሉ በማስወገድ ወንጌል ወደ ልብ መንገድ ሲያገኝ፣ ያኔ የእግዚአብሔርን መዳን ለመቀበል ዝግጅት ይደረጋል።

ዮሐንስ የሰጣቸው አጠቃላይ ማስጠንቀቂያዎችና ምክሮች እዚህ አሉ። በደለኛ የሆነው፣ የተበላሸው የሰው ልጅ ዘር የእፉኝት ትውልድ ሆኗል፤ ለእግዚአብሔር የተጠላ፣ እንዲሁም እርስ በርስ የሚጠላለፍ ነው። ከሚመጣው ቁጣ ለማምለጥ ከንስሓ በቀር ምንም መንገድ የለም፤ የአእምሯችን ለውጥም በኑሮአችን ለውጥ መታየት አለበት። በልብም ሆነ በሕይወት በእውነት ቅዱሳን ካልሆንን፣ የሃይማኖት መግለጫችንና ከእግዚአብሔርና ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ያለን ግንኙነት በፍጹም አይጠቅመንም፤ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ ካላፈራን ጥፋታችንም እጅግ የከፋ ይሆናል።

መጥምቁ ዮሐንስ ለተለያዩ የሰዎች ዓይነቶች መመሪያዎችን ሰጥቷል። ንስሓን እንደሚገቡ የሚናገሩና ቃል የሚገቡ ሰዎች እንደየቦታቸውና እንደየሁኔታቸው በለውጥ ማሳየት አለባቸው። ወንጌል ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይሻም፤ ዓላማውም የምንችለውን ያህል መልካም ነገር እንድናደርግና ለሁሉም ሰዎች ፍትሐዊ እንድንሆን ነው። ሰዎችን ኢፍትሐዊ ትርፍ እንዲተው የሚያደርገው ተመሳሳይ መርህ፣ በስህተት የተገኘውን ነገር እንዲመልሱ ያደርጋል። ዮሐንስም ወታደሮችን ግዴታቸውን ነግሯቸዋል። ሰዎች ከሥራቸው ፈተናዎች ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው ይገባል። እነዚህ መልሶች የጠያቂዎቹን የአሁኑን ግዴታ የገለጹ ከመሆናቸውም በላይ፣ ወዲያውኑም ለቅንነታቸው መፈተኛ ሆነዋል። ያለ እውነተኛ ንስሓ ማንም የክርስቶስን መዳን መቀበል ስለማይችል፣ የዚህም ንስሓ ማስረጃና ውጤቶች እዚህ ተዘርዝረዋል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፥ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስም በኢጡርያስ በጥራኮኒዶስም አገር የአራተኛ… አማርኛ ENGNIV In the fifteenth year of the reign of Tiberius Caesar–when Pontius Pilate was governor of Judea, Herod tetrarch of Gali… English BCV ጢባርዮስ ቄሳር ካብ ዝነግስ፥ ኣብ መበል ዓሰርተ ሓሙሽተ ዓመት፥ ጲላጦስ ጴንጤናዊ ኣብ ይሁዳ ኽገዝእ እንተሎ፥ ሄሮድስ ኣብ ገሊላ፥(ሀ) ፊልጶስ ሓዉ ኣብ ኢጡርያስን ኣብ ሃገር ጥራኮኒዶስን፥… ትግርኛ GAZBIB Xiberiyos mootichi mo'ee waggaa kudha shanaffaatti, Phonxos Philaaxos biyya Yihudaa bulche; Herodis immoo biyya Galiila… Afaan Oromoo BCV GIZ ወአመ ዐሠርቱ ወኀምስቱ ዓመተ መንግሥቱ ለጢባርዮስ ቄሳር እንዘ ጲላጦስ ጰንጤናዊ መልአከ ይሁዳ ወሄሮድስ ንጉሥ ላዕለ ገሊላ ወፊልጶስ እኁሁ መልአከ ኢጡርያስ ወለብሔረ ጥራኮኒዶስ ወሊሳንዩስ … giz GAZGAZ Xiberiyos mootichi mo'ee waggaa kudha shanaffaatti, Phonxos Philaaxos biyya Yihudaa bulche; Herodis immoo biyya Galiila… Afaan Oromoo BCV aksum ጢባርዮስ ቄሳር ካብ ዝነግስ፥ ኣብ መበል ዓሰርተ ሓሙሽተ ዓመት፥ ጲላጦስ ጴንጤናዊ ኣብ ይሁዳ ኽገዝእ እንተሎ፥ ሄሮድስ ኣብ ገሊላ፥(ሀ) ፊልጶስ ሓዉ ኣብ ኢጡርያስን ኣብ ሃገር ጥራኮኒዶስን፥… ትግርኛ SWAHSUV Mwaka wa kumi na tano wa kutawala kwake Kaisari Tiberio, Pontio Pilato alipokuwa liwali wa Uyahudi, na Herode mfalme wa… Kiswahili