1ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፥ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስም በኢጡርያስ በጥራኮኒዶስም አገር የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ሊሳኒዮስም በሳቢላኒስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆነው ሳሉ፥
2ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።
3በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ፦ “የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ፥ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፡” ተብሎ እንደ ተጻፈ፡ ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ።
7ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?
8እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን፡ ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል፡ እላችኋለሁና።
9አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።”
10ሕዝቡም፦ “እንግዲህ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር።
11መልሶም፦ “ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፥ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ፡” ይል ነበር።
12ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ “መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሉት።
13“ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ፡” አላቸው።
14ጭፍሮችም ደግሞ፦ “እኛ ደግሞ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ “በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ፡” አላቸው።
15ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ፦ “ይህ ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው ሲያስቡ ነበር፥
16ዮሐንስ መልሶ፦ “እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤
17መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፡” አላቸው።
18ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤
19የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥
20ይህን ደግሞ ከሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አገባው።
21ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥
22መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።
23ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥
24የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥
25የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤሲሊም ልጅ፥ የናጌ ልጅ፥
26የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮዳ ልጅ፥
27የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥
28የሚልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ የዮሳስ ልጅ፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥
29የዮሴዕ ልጅ፥ የኤልዓዘር ልጅ፥ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥
30የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥
31የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ፥ የዳዊት ልጅ፥
32የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ የነአሶን ልጅ፥
33የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የአሮኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥ የፋሬስ ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥
34የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥ የናኮር ልጅ፥
35የሴሮህ ልጅ፥ የራጋው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የአቤር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥
36የቃይንም ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜህ ልጅ፥
37የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥ የመላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥
38የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ።