የሉቃስ ወንጌል 10

AMHNIVአማርኛ42 ጥቅሶች6:46 አዳምጥ
አዳምጥ 6:46 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መርጦ ሾመ፤ ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤

2እንዲህም አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂት ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ቦታ እንዲልክ ለምኑት።

3እንግዲህ ሂዱ፤ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ።

4ኰረጆ ወይም ከረጢት፣ ወይም ጫማ አትያዙ፤ በመንገድ ላይም ለማንም ሰላምታ አትስጡ።

5“ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ አስቀድማችሁ፣ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ፤

6የሰላም ሰው በዚያ ካለ፣ ሰላማችሁ ያርፍበታል፤ አለዚያም ሰላማችሁ ለእናንተው ይመለሳል።

7ያቀረቡላችሁን ሁሉ እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያ ቤት ተቀመጡ፤ የሚሠራ ደመወዝ ማግኘት ይገባዋልና። ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ።

8“ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ከተቀበሏችሁ፣ ያቀረቡላችሁን ብሉ።

9በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሏቸው።

10ነገር ግን ወደ አንድ ከተማ ገብታችሁ ካልተቀበሏችሁ፣ ወደ አደባባዩ ውጡና እንዲህ በሉ፤

11‘በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች ይህን ዕወቁ።’

12እላችኋለሁ፤ በዚያን ዕለት ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ቀላል ይሆንላታል።

13“ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዲ በእናንተ የተደረገው ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር።

14ነገር ግን በፍርድ ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።

15አንቺም ቅፍርናሆም፣ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ።

16“እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።”

17ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት።

18እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ።

19እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም።

20ይሁን እንጂ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”

21በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ሁሉ ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፣ አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።

22“ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።”

23ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤

24እላችኋለሁና፤ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም።”

25እነሆም አንድ ቀን፣ አንድ ሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው።

26ኢየሱስም፣ “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነበዋለህ?” ሲል መለሰለት።

27ሰውየውም መልሶ፣ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” አለው።

28ኢየሱስም፣ “በትክክል መልሰሃል፤ አንተም እንደዚሁ አድርግ፤ በሕይወት ትኖራለህ” አለው።

29ሰውየውም ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው።

30ኢየሱስም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው፤ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ።

31አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቍልቍል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ አለፈ።

32ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ አለፈ።

33አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤

34ቀርቦም ቊስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው።

35በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጪ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው።

36“እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?”

37ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ። ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።

38ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ መንገድ ሲሄዱ፣ ኢየሱስ ወደ አንድ መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤቷ ተቀበለችው።

39እርሷም ማርያም የተባለች እኅት ነበረቻት፤ ማርያምም ቃሉን እየሰማች በጌታ እግር ሥር ተቀምጣ ነበር።

40ማርታ ግን በሥራ ብዛት ትባክን ነበርና ወደ እርሱ ቀርባ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኅቴ ሥራውን ለእኔ ብቻ ጥላ ስትቀመጥ ዝም ትላለህን? እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” አለችው።

41ጌታ ግን እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ማርታ፣ ማርታ፤ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ትዋከቢአለሽም፤

42የሚያስፈልገው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ማርያም እኮ የሚሻለውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእርሷ አይወሰድም።”

ማብራሪያ

፲፥፩-፲፮ ክርስቶስ ሰባውን ደቀ መዛሙርት እርስ በእርሳቸው እንዲበረታቱና እንዲደፋፈሩ ዘንድ ሁለት ሁለት አድርጎ ሰደዳቸው። የወንጌል አገልግሎት ሰዎችን ክርስቶስን እንደ ልዑልና እንደ አዳኝ እንዲቀበሉ ይጠራል፤ እርሱም ታማኝ አገልጋዮቹን ወደሚልካቸው ስፍራዎች ሁሉ በመንፈሱ ኃይል በእርግጥ ይመጣል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ የሚቀበሉ ሰዎች ፍርድ እጅግ አስፈሪ ይሆናል። የክርስቶስን ታማኝ አገልጋዮችን የሚንቁ፣ በእነርሱ ላይ አሳንስው የሚያዩ እና በንቀት የሚመለከቷቸው፣ የእግዚአብሔርንና የክርስቶስን እንደ ንቀው ይቆጠራሉ።

10:17-24

በሰይጣን ላይ የምናገኛቸው ድሎች ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ በተገኘ ኃይል የሚገኙ ናቸው፤ ምስጋናውም ሁሉ ለእርሱ ሊሆን ይገባዋል። ነገር ግን የብዙዎችን ጥፋት ከሆነው ከመንፈሳዊ ትዕቢት እንጠንቀቅ። ጌታችን የብዙ ነፍሳት መዳን ተስፋ ሲያይ ደስ አለው። ያ የደስታ ሰዓት በተለይ ሊታሰብበት ይገባ ነበር፤ እንደዚህ ያሉት ጥቂቶች ነበሩና እርሱ የሐዘን ሰው ነበር። ሰይጣን ሲወድቅ ባየበትና የአገልጋዮቹንም መልካም ስኬት በሰማበት በዚያ ሰዓት ደስ አለው። እርሱ ትዕቢተኞችን ሁልጊዜ ተቃውሟል፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። በወልድ እግዚአብሔር ትምህርት፣ እርዳታና በረከት ላይ በቀጥታ የምንመካ በሆንን መጠን፣ የአብንም የወልድንም እውቀት ይበልጥ እናገኛለን፤ የመለኮታዊውን አዳኝ ክብር በማየትና ቃሉንም በመስማት ይበልጥ እንባረካለን፤ ዓላማውንም በማስፋፋት ይበልጥ ጠቃሚ እንሆናለን።

10:25-37 ስለ ዘላለማዊ ሕይወትና ወደ እርሱ ስለሚወስደው መንገድ በግድየለሽነት የምንናገር ከሆነ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ እንጠራለን። የመመለስ ጸጋ ተካፋይ ያልሆነ ማንም ሰው ንጹሕ በሆነ መንፈሳዊ ፍቅር እግዚአብሔርንና ባልንጀራውን ሊወድ አይችልም። ነገር ግን የሰው የትዕቢት ልብ እነዚህን ሕሊናዊ ማሳመኛዎች አጥብቆ ይዋጋል። ክርስቶስ በደግ ሳምራዊ ስለተረዳ መከራ ላይ ስለነበረ አንድ ምስኪን አይሁዳዊ ምሳሌ ሰጠ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6