1እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦
2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው፦ ‘ማንም ሰው ከሥጋው ፈሳሽ ነገር ቢወጣ፥ ስለሚፈስሰው ነገር ርኩስ ነው።
3ስለሚፈስሰው ነገር ርኵስነቱ ይህ ነው፤ ፈሳሹ ነገር ከሥጋው ቢፈስስ ወይም ከመፍሰሱ ቢቆም፥ ርኩስ መሆኑ ነው።
4“ ‘ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው፤ የሚቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።
5መኝታውንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
6ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በተቀመጠበት ነገር ላይ የሚቀመጥበት ሰው ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
7“ ‘ፈሳሽ ነገር ያለበትን የሰውን ሥጋ የሚነካ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
8“ ‘ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በንጹሕ ሰው ላይ ቢተፋ፥ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
9“ ‘ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ነው።
10ከበታቹም ያለውን ነገር የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
11“ ‘ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው እጁን በውኃ ሳይታጠብ የሚነካው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
12“ ‘ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚነካውን የሸክላ ዕቃ ይስበሩት፤ የእንጨቱም ዕቃ ሁሉ በውኃ ይታጠብ።
13“ ‘ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል፤ ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል።
14በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ይመጣል፥ ለካህኑም ይሰጣቸዋል።
15ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል።
16“ ‘የማንም ሰው ዘር ከእርሱ ቢወጣ፥ ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
17ዘር የነካው ልብስ ሁሉ ቁርበትም ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
18ወንዱ በሴቲቱ ቢደርስባት ሁለቱ በውኃ ይታጠባሉ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩሶች ናቸው።
19“ ‘ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።
20“ ‘መርገምም ስትሆን የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።
21መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው።
22የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
23በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።
24“ ‘ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው።
25“ ‘ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ ርኩስ ናት።
26ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በመርገምዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ መርገምዋ ርኵስነት ርኵስ ነው።
27እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው።
28“ ‘ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች።
29በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች።
30ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል።
31“ ‘እንዲሁም በእነርሱ መካከል ያለችውን ማደሪያዬን ባረከሱ ጊዜ፥ በርኵስነታቸው እንዳይሞቱ የእስራኤልን ልጆች ከርኵስነታቸው ለያቸው።’ ”
32ፈሳሽ ነገር ላለበት ሰው፥ ይረክስም ዘንድ ዘሩ ለሚወጣበት ሰው፥
33በመርገምዋም ለታመመች፥ ፈሳሽም ነገር ላለባቸው ለወንድም ለሴትም፥ የረከሰችንም ሴት ለሚገናኝ ሰው ሕጉ ይኸው ነው።