1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2“በእርግጥ እናንተ ዓይነተኞች ሰዎች ናችሁ፤ ጥበብም ከእናንተ ጋር ይሞታል።
3ነገር ግን እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ማስተዋል አለኝ፤ ከእናንተም የማንስ አይደለሁም፤ እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው?
4“እግዚአብሔርን የጠራሁ እርሱም የመለሰልኝ እኔ፡ ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፤ ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል።
5ተዘልሎ በሚቀመጥ ሰው አሳብ መከራ ይናቃል፤ ነገር ግን እግሩን ሊያድጠው ተዘጋጅቶአል።
6የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዘልለው ተቀምጠዋል፤ እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል።
7“አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።
9የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፡ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
10የሕያዋን ሁሉ ነፍስ፡ የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናት።
11ምላስ መብልን እንደሚቀምስ፥ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን?
12በሽምግልና ጊዜ ጥበብ፥ በዘመንስ ርዝመት ማስተዋል ይገኛል።
13“በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፤ ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።
14እነሆ፥ ይፈርሳል፥ የፈረሰውም ተመልሶ አይሠራም፤ በሰውም ቢዘጋበት የሚከፍትለት የለም።
15እነሆ፥ ውኆቹን ይከለክላል፥ እነርሱም ይደርቃሉ፤ እንደ ገና ይሰድዳቸዋል፥ ምድሪቱንም ይገለብጣሉ።
16ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፤ የሚስተውና የሚያስተው ለእርሱ ናቸው።
17መካሮችንም እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ፈራጆችንም ያሳብዳል።
18የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥ ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል።
19ካህናትን እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል።
20ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥ የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል።
21በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥ የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል።
22ጥልቅ ነገር ከጨለማ ይገልጣል፥ የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል።
23አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፤ አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል።
24ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ይወስዳል፥ መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል።
25ብርሃንም ሳይኖር በጨለማ ይርመሰመሳሉ፤ እንደ ሰካራም ይቅበዘበዛሉ።