ትንቢተ ኤርምያስ 44

AMHEVGአማርኛ30 ጥቅሶች7:40 አዳምጥ
አዳምጥ 7:40 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በግብፅ ምድር በሚግዶልና በጣፍናስ በሜምፎስም በጳትሮስም አገር ስለ ተቀመጡ አይሁድ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው።

2የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ አይታችኋል፤ እነሆ፥ ዛሬ ባድማ ሆነዋል፥ የሚቀመጥባቸውም የለም።

3ይህም የሆነው ያስቈጡኝ ዘንድ ስላደረጉት ክፋት፥ ለማያውቁአቸውም ለሌሎች አማልክት ያጥኑ ዘንድ ያመልኩአቸውም ዘንድ ስለሄዱ ነው።

4በማለዳም ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ሰደድሁባችሁና፦ እንደዚህ እንደ ጠላሁት ያለ ርኩስ ነገር አታድርጉ፡ አልኋችሁ።

5ነገር ግን አልሰሙም ከክፋታቸውም ተመልሰው ለሌሎች አማልክት እንዳያጥኑ ጆሮአቸውን አላዘነበሉም።

6ስለዚህ መዓቴና ቍጣዬ ፈሰሱ፥ በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ነደዱ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ፈረሱ ባድማም ሆኑ።

7አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን ቅሬታ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ብላቴናንና ሕፃንን ከመካከላችሁ ታጠፉ ዘንድ ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ?

8ሰውነታችሁንም ታጠፉ ዘንድ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ ትሆኑ ዘንድ፥ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብፅ ምድር ለሌሎች አማልክት በማጠናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ?

9በውኑ በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያደረጉትን የአባቶቻችሁን ክፋት፥ የይሁዳንም ነገሥታት ክፋት፥ የሚስቶቻቸውንም ክፋት፥ የእናንተንም ክፋት፥ የሚስቶቻችሁንም ክፋት ረስታችሁታልን?

10እስከ ዛሬ ድረስ አልተዋረዱም አልፈሩምም፥ በእናንተና በአባቶቻችሁም ፊት ባኖርሁት ሕጌና ሥርዓቴ አልሄዱም።

11ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይሁዳን ሁሉ አጠፋ ዘንድ ፊቴን ለክፋት በላያችሁ አደርጋለሁ።

12ወደ ግብፅም ይገቡ ዘንድ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ቅሬታ እወስዳለሁ፥ ሁሉም ይጠፋሉ፥ በግብፅም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለመደነቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ።

13ኢየሩሳሌምንም እንደ ቀጣሁ፥ እንዲሁ በግብፅ ምድር የሚኖሩትን በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እቀጣለሁ።

14በዚያ ለመቀመጥ ወደ ግብፅ ምድር ከሄዱ፥ ወደ ይሁዳ አገር ተመልሰው በዚያ ይቀመጡ ዘንድ ከሚወድዱ ከይሁዳ ቅሬታ ወገን የሚያመልጥና የሚቀር ወደዚያም የሚመለስ የለም፤ ከሚያመልጥም በቀር ማንም አይመለስም።

15ሚስቶቻቸውም ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ሰዎች ሁሉ በዚያም የቆሙ ሴቶች ሁሉ፥ በግብፅ ምድር በጳትሮስ የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ መለሱለት እንዲህም አሉ፦

16አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን ቃል አንሰማህም።

17ነገር ግን እኛና አባቶቻችን ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞች በኢየሩሳሌም አደባባይ እናደርገው እንደ ነበረ፥ ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ የመጠጥንም ቍርባን እናፈስስላት ዘንድ ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በእርግጥ እናደርጋለን፤ በዚያን ጊዜም እንጀራ እንጠግብ ነበር፥ መልካምም ይሆንልን ክፉም አናይም ነበር።

18ለሰማይ ንግሥት ማጠንን ለእርስዋም የመጠጥን ቍርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፥ እኛ በሁሉ ነገር ተቸግረናል፥ በሰይፍና በራብ አልቀናል።

19እኛስ ለሰማይ ንግሥት ባጠንንላት የመጠጥንም ቍርባን ባፈሰስንላት ጊዜ፥ በውኑ ያለ ባሎቻችን ምስልዋን ለማበጀት እንጐቻ አድርገንላት ኖሮአልን? የመጠጥንም ቍርባን አፍስሰንላት ኖሮአልን?

20ኤርምያስም ይህን ቃል ለመለሱለት ሕዝብ ሁሉ፥ ለወንዶቹና ለሴቶቹ ለሕዝቡም ሁሉ፥ መለሰላቸው እንዲህም፡ አለ፦

21እናንተና አባቶቻችሁ ነገሥታቶቻችሁም አለቆቻችሁም የምድርም ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያጠናችሁትን ዕጣን እግዚአብሔር ያሰበው በልቡም ያኖረው አይደለምን?

22እግዚአብሔርም ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኵሰት ይታገሥ ዘንድ አልቻለም፤ ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ መደነቂያም መረገሚያም ሆናለች ዛሬም እንደ ሆነ የሚኖርባት የለም።

23ስላጠናችሁ፥ በእግዚአብሔርም ላይ ስለ በደላችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልሰማችሁ፥ በሕጉና በሥርዓቱም በምስክሩም ስላልሄዳችሁ፥ ስለዚህ ዛሬ እንደ ሆነ ይህች ክፉ ነገር አግኝታችኋለች።

24ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ለሴቶቹም ሁሉ እንዲህ አለ፦ በግብፅ ምድር የምትኖሩ ይሁዳ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

25የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ፦ ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ የመጠጥንም ቍርባን እናፈስስላት ዘንድ የተሳልነውን ስእለታችንን በእርግጥ እንፈጽማለን፡ አላችሁ፥ በእጃችሁም አደረጋችሁት፤ እንግዲህ ስእለታችሁን አጽኑ፥ ስእለታችሁንም ፈጽሙ።

26እናንተ በግብፅ ምድር የምትኖሩ ይሁዳ ሁሉ፥ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ተብሎ እንዳይጠራ፥ እነሆ፥ በታላቅ ስሜ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

27እነሆ፥ ለመልካም ሳይሆን ለክፋት እተጋባቸዋለሁ፤ በግብፅም ምድር ያሉት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ያልቃሉ።

28ከሰይፍም የሚያመልጡ ጥቂት ሰዎች ሆነው ከግብፅ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ፤ ሊቀመጡም ወደ ግብፅ ምድር የገቡት የይሁዳ ቅሬታ ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማናችን ቃል እንዲጸና ያውቃሉ።

29ቃሌም በላያችሁ ለክፋት እንዲጸና ታውቁ ዘንድ በዚህች ስፍራ እንድቀጣችሁ ምልክታችሁ ይህ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር።

30እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነው ነፍሱንም ለፈለገው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የግብጹን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ለጠላቶቹ ነፍሱንም ለሚፈልጉ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።

ማብራሪያ

፵፬:፩-፲፬ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ውድመትን ስላመጡት ኃጢአቶች አይሁድን ያስታውሳቸዋል። ሰዎችን ስለ ኃጢአት አደገኛነት በሙሉ ቁም ነገር ማስጠንቀቅ ይገባናል። 'ወይ! ይህን አታድርጉት!' ልንል ይገባል። እግዚአብሔርን የምትወዱ ከሆነ፣ እርሱን ያስቆጣዋልና አታድርጉት፤ የራሳችሁን ነፍሳት የምትወዱ ከሆነ ደግሞ፣ ያጠፋታልና አታድርጉት። በፈተና ሰዓት ሕሊናችን ይህንን ለእኛ ያድርግልን።

እግዚአብሔር ወደ ከለዳውያን ምድር የላካቸው አይሁድ እዚያ በእግዚአብሔር ጸጋ ኃይል ከጣዖት አምልኮ ተገፈፉ፤ ነገር ግን በገዛ ጠማማ ፈቃዳቸው ወደ ግብፅ ምድር የሄዱት፣ እዚያ ከምንጊዜውም በላይ ከጣዖት አምልኳቸው ጋር ይበልጥ ተጣበቁ። ምክንያት ሳይኖርብን ወይም ጥሪ ሳናገኝ ራሳችንን ወደ ፈተና ስፍራዎች ስንወረውር፣ እግዚአብሔር ለራሳችን ሊተወን ፍትሐዊ ነው። እኛ በእግዚአብሔር ላይ ብንሄድ እርሱም እኛ ላይ ይሄዳል። ሰዎች የሚጋለጡባቸው እጅግ አስከፊ መከራዎች የሚከሰቱት የቀረበውን ድነት ችላ በማለታቸው ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

ENGNIV This word came to Jeremiah concerning all the Jews living in Lower Egypt–in Migdol, Tahpanhes and Memphis– and in Upper… English BCV እግዚኣብሄር ብዛዕባ እቶም ኣብ ሃገር ግብፂ ዝነበሩ፥ ብዛዕባ እቶም ኣብ ከተማታት ሚግዶል፥ ጣፍናስ፥ ሜምፎስ፥ ጳትሮስ ተቐሚጦም ዝነበሩ ኣይሁድ ናብ ኤርሚያስ ዝመፀ ቓል እዙይ እዩ፦ ትግርኛ GAZBIB Waa'ee Yihudoota warra biyya Gibxii keessa mandara Miigdol, Taahafenee, Nofii fi Phaaxros keessa jiraatan hundumaaf dub… Afaan Oromoo BCV GIZ ቃል ዘኮነ ኀበ ኤርምያስ እምኀበ እግዚአብሔር ከመ ይትነበይ ወኀበ ኵሎሙ አይሁድ እለ ይነብሩ ውስተ ግብፅ ወእለ ይነብሩ ውስተ ጣፍናስ ወመግደሎ ወውስተ ሜምፎስ ወውስተ ምድር ፋቱራ፤ giz GAZGAZ Waa'ee Yihudoota warra biyya Gibxii keessa mandara Miigdol, Taahafenee, Nofii fi Phaaxros keessa jiraatan hundumaaf dub… Afaan Oromoo BCV aksum እግዚኣብሄር ብዛዕባ እቶም ኣብ ሃገር ግብፂ ዝነበሩ፥ ብዛዕባ እቶም ኣብ ከተማታት ሚግዶል፥ ጣፍናስ፥ ሜምፎስ፥ ጳትሮስ ተቐሚጦም ዝነበሩ ኣይሁድ ናብ ኤርሚያስ ዝመፀ ቓል እዙይ እዩ፦ ትግርኛ AMHNIV በግብፅ ሰሜናዊ ክፍል በሚግዶል፣ በጣፍናስና በሜምፎስ እንዲሁም በግብፅ ደቡባዊ ክፍል ስለሚኖሩት የአይሁድ ሕዝብ እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤ አማርኛ SWAHSUV Neno lililomjia Yeremia, katika habari za Wayahudi wote waliokaa katika nchi ya Misri, waliokaa Migdoli, na Tahpanesi, … Kiswahili