1ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “መድረኮቹ እንዲናወጡ፣ ጒልላቶቹን ምታ፣ በሕዝቡም ሁሉ ራስ ላይ ሰባብራቸው፤ የቀሩትን በሰይፍ እገድላቸዋለሁ፤ ከእነርሱ አንድም ሰው አይሸሽም፤ ቢሸሽም የሚያመልጥ የለም።
2መቃብር በጥልቀት ቈፍረው ቢወርዱም፣ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይ ቢወጡም፣ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ።
3በቀርሜሎስ ጫፍ ላይ ቢሸሸጉም፣ አድኜ ፈልጌ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ እይዛቸዋለሁም፤ በጥልቅ ባሕር ውስጥ ከእኔ ቢሸሸጉም፣ በዚያ እባቡ እንዲነድፋቸው አዘዋለሁ፤
4በጠላቶቻቸው ተነድተው ለምርኮ ቢወሰዱም፣ በዚያ እንዲገድላቸው ሰይፍን አዛለሁ፤ ለመልካም ሳይሆን ለክፉ፣ ዓይኔን በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ።
5ጌታ፣ እግዚአብሔር ጸባኦት፣ ምድርን ይዳስሳል፤ እርሷም ትቀልጣለች፤ በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የምድር ሁለመና እንደ ዐባይ ወንዝ ይነሣል፤ እንደ ግብጽ ወንዝም ይወርዳል።
6መኖሪያውን በሰማይ የሚሠራ፣ መሠረቱንም በምድር የሚያደርግ፣ የባሕርን ውሃ የሚጠራ፣ በምድርም ገጽ ላይ የሚያፈስ፣ እርሱ ስሙ እግዚአብሔር ነው።
7“እናንት እስራኤላውያን፣ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር “እስራኤልን ከግብጽ፣ ፍልስጥኤማውያንን ከከፍቶር፣ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?
8“እነሆ፤ የጌታ እግዚአብሔር ዐይኖች፣ በኀጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፤ ከምድር ገጽ፣ ፈጽሜ አጠፋዋለሁ፤ የያዕቆብን ቤት ግን፣ ሙሉ በሙሉ አልደመስስም፤” ይላል እግዚአብሔር።
9“እነሆ፤ ትእዛዝ እሰጣለሁ፤ እህል በወንፊት እንደሚነፋ፣ የእስራኤልን ቤት፣ በሕዝብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።
10በሕዝቤ መካከል ያሉ፣ ‘ክፉ ነገር አያገኘንም ወይም አይደርስብንም’ የሚሉ፣ ኀጢአተኞች ሁሉ፣ በሰይፍ ይሞታሉ።
11“በዚያ ቀን፣ የወደቀውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፤ የተሰበረውን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውን ዐድሳለሁ፤ ቀድሞ እንደነበረም አድርጌ እሠራዋለሁ፤
12ስለዚህ የኤዶምን ትሩፍ፣ በስሜ የተጠሩትንም ሕዝቦች ሁሉ ይወርሳሉ፤” ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ዐጫጁ ዐጭዶ ሳይጨርስ፣ ዐራሹ በላዩ የሚደርስበት፣ ችግኝ ተካዩም ገና ተክሎ ሳይጨርስ፣ ወይን ጨማቂው የሚደርስበት ጊዜ ይመጣል፤ አዲስ የወይን ጠጅ ከተራሮች ይንጠባጠባል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ ይፈሳል።
14የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ፤ እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ። የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤ አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።
15እስራኤልን በገዛ ምድራቸው እተክላቸዋለሁ፤ ከሰጠኋቸውም ምድር፣ ዳግመኛ አይነቀሉም” ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።