ትንቢተ አሞጽ 8

AMHEVGአማርኛ14 ጥቅሶች2:39 አዳምጥ
አዳምጥ 2:39 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ እነሆም፥ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነበረ።

2እርሱም፦ “አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው?” አለኝ። እኔም፦ “የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው፡” አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ፦ “ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም።

3የመቅደሱ ዝማሬ በዚያ ቀን ዋይታ ይሆናል፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ “የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል።”

4ችጋረኛውን የምትውጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ እናንተ ሆይ፦

5“እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥

6ድሀውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መቼ ያልፋል?” የምትሉ እናንተ ሆይ፥ ይህን ስሙ።

7እግዚአብሔር በያዕቆብ ክብር እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ “ሥራቸውን ሁሉ ለዘላለም ምንም አልረሳም።

8በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርስዋም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ሙላዋም እንደ ወንዙ ትነሣለች፤ እንደ ግብፅም ወንዝ ትነሣለች ደግሞም ትወርዳለች።

9በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለሁ።

10ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬአችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ ማቅንም በወገብ ሁሉ፥ ራስ መንጨትንም በሁሉ ላይ አመጣለሁ፤ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ፥ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ።

11“እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።

12ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፥ አያገኙትምም።

13በዚያ ቀን መልካካሞች ደናግል ጐበዛዝትም በጥም ይዝላሉ።

14በሰማርያ ኃጢአት የሚምሉና፦ ‘ዳን ሆይ፥ ሕያው አምላክህን!’ ደግሞ፦ ‘ሕያው የቤርሳቤህን መንገድ!’ ብለው የሚሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ደግሞም አይነሡም።”

ማብራሪያ

8:1-3 አሞጽ የተሰበሰበውንና ለመበላት የተዘጋጀውን የበጋ ፍሬ ቅርጫት አየ፤ ይህም የሚያመለክተው ሕዝቡ ለመጥፋት የደረሰ መሆኑንና የእግዚአብሔር የትዕግሥት ዘመን ፍጻሜው እየቀረበ እንደሆነ ነው። እንዲህ ያሉ የበጋ ፍሬዎች እስከ ክረምት ድረስ አይቆዩም፥ ነገር ግን ወዲያውኑ መበላት አለባቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ፍርዶች የእግዚአብሔርን ጽድቅም ሆነ የራሳቸውን ዓመፀኝነት ከእነርሱ ዘንድ ምንም ዓይነት እውቅና አያስገኙም። ኃጢአተኞች ንስሐ መግባትን ከዕለት ወደ ዕለት ያዘገያሉ፥ ምክንያቱም ጌታ ፍርዶቹን እንደዚህ እያዘገየ ነው ብለው ያስባሉና።

8:4-10 የሀገሩ ባለጸጎችና ኃያላን በጭቆና እጅግ በጣም ጥፋተኞች ነበሩ፤ እንደዚሁም በጣዖት አምልኮ ግንባር ቀደም ነበሩ። የሰንበትና የአዲስ ወር እገዳዎች ሰልችቷቸው ነበር፤ ምክንያቱም በእነዚያ ቀናት የተለመደ ሥራ መሥራት ስለማይቻል እንዲያልፉላቸው ይመኙ ነበር። ይህ ደግሞ ክርስቲያን ነን ከሚሉ ብዙዎች ባህርይ ነው። የሰንበት ቀንና የሰንበት ሥራ ሥጋ ለባሽ ለሆኑ ልቦች ከባድ ሸክም ናቸው። ወይ ይረክሳል አሊያም አሰልቺ ቀን ተደርጎ ይቆጠራል። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በህብረት ከመሆን የተሻለ ጊዜያችንን ልናሳልፍ እንችላለንን? በሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ላይ ሳሉ፣ ስለ ንግድ ሥራቸው ያስቡ ነበር። ቅዱስ ተግባራት ሰልችቷቸው ነበር፤ ምክንያቱም ዓለማዊ ሥራቸው በዚያን ጊዜ ቆሞ ነበርና።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6