ትንቢተ አሞጽ 6

AMHNIVአማርኛ14 ጥቅሶች2:50 አዳምጥ
አዳምጥ 2:50 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በጽዮን ተዘልላችሁ የምትቀመጡ፣ በሰማርያ ተራራ ያለ ሥጋት የምትኖሩ፣ የእስራኤልም ሕዝብ ለርዳታ ወደ እናንተ የሚመጡባችሁ፣ እናንት የአሕዛብ አለቆች ሆይ፤ ወዮላችሁ!

2ወደ ካልኔ ሂዱ፤ እርሱንም ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ወደ ፍልስጥኤም ከተማ ወደ ጌትም ውረዱ፤ እነዚህ ከሁለቱ መንግሥታቶቻችሁ ይሻላሉን? የምድራቸውስ ስፋት ከእናንተ ይበልጣልን?

3ክፉውን ቀን ለምታርቁ፣ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ ወዮላችሁ!

4በዝሆን ጥርስ ባጌጠ ዐልጋ ላይ ለምትተኙ፤ በድንክ ዐልጋችሁ ላይ ለምትዝናኑ፣ ከበጎች መንጋ ጠቦትን፣ ከጋጣም ጥጃን ለምትበሉ፤

5ባልተቃኘ በገና ለምትዘፍኑ፣ በሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ለምትሹ፣

6በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፣ ምርጥ ሽቱም ለምትቀቡ፣ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ወዮላችሁ!

7ስለዚህ እናንተ በመጀመሪያ በምርኮ ከሚወሰዱት መካከል ናቸሁ፤ መፈንጠዛችሁና መዝናናታችሁም ያበቃል።

8ጌታእግዚአብሔር “የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፤ ምሽጎቹንም ጠልቻለሁ፤ ከተማዪቱንና በውስጥዋ ያለውን ሁሉ፣ አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል በራሱ ምሎአል፤ ይላል የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር።

9በአንድ ቤት ውስጥ ዐሥር ሰዎች ቢቀሩ እነርሱም ይሞታሉ።

10በድኖቹንም ከቤት አውጥቶ ማቃጠል ያለበት አንድ ዘመድ መጥቶ ተደብቆ ያለውን ሰው፣ “ከአንተ ጋር የቀረ ሌላ ሰው አለን?” ሲለው፣ እርሱም “የለም” ይለዋል፤ ከዚያም በኋላ፣ “ዝም በል፤ የእግዚአብሔርን ስም መጥራት አይገባንም” ይለዋል።

11እነሆ፤ እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጥቶአልና፤ ታላላቅ ቤቶችን ያወድማቸዋል፤ ትንንሾቹንም ያደቅቃቸዋል።

12ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይሮጣሉን? ሰውስ እዚያ ላይ በበሬ ያርሳልን? እናንተ ግን ፍትሕን ወደ መርዝነት፣ የጽድቅንም ፍሬ ወደ መራራነት ለወጣችሁ።

13እናንተ ሎዶባርን በማሸነፋችሁ ደስ ያላችሁ፣ “ቃርናይምን በራሳችን ብርታት ይዘናል” የምትሉ፣

14ሁሉን የሚገዛ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እነሆ፤ እኔ ከሐማት መግቢያ እስከ ዓረባ ሸለቆ ድረስ፣ የሚያስጨንቃችሁን ሕዝብ፣ በእናንተ ላይ አስነሣለሁ።”

ማብራሪያ

6:1-7 ለሥጋቸው ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች ለራሳቸው መልካም የሚያደርጉ ይመስላሉ፤ ነገር ግን በዚህ ክፍል ውስጥ ምቾታቸው ምን እንደሆነና ወዮላቸውም ምን እንደሆነ ተገልጾልናል። እዚህ ላይ እግዚአብሔር የሚጠይቅባቸውን ትዕቢት፣ መዘናጋትና ሥጋዊ ምኞት ገለጻ ቀርቦአል። ቸልተኛ ኃጢአተኞች በየትኛውም ስፍራ በአደጋ ውስጥ ናቸው፤ ነገር ግን በጽዮን ውስጥ ያሉት፣ የደነዘዙት፣ በከንቱ የሚተማመኑትና መብቶቻቸውን አላግባብ የሚጠቀሙት እጅግ በከፋ አደጋ ውስጥ ናቸው። ሆኖም በኃጢአት ውስጥ የሚኖሩና ከዓለም ጋር የሚስማሙ ብዙዎች ራሳቸውን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6