ትንቢተ አሞጽ 5

AMHEVGአማርኛ27 ጥቅሶች4:16 አዳምጥ
አዳምጥ 4:16 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእናንተ ላይ ለሙሾ የማነሣውን ይህን ቃል ስሙ።

2የእስራኤል ድንግል ወደቀች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሣም፤ በምድርዋ ላይ ተጣለች፥ የሚያስነሣትም የለም።

3ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላልና፦ “ሺህ ከሚወጣባት ከተማ መቶ ይቀርላታል፥ መቶም ከሚወጣባት ከተማ ለእስራኤል ቤት አሥር ይቀርላታል።”

4እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና፦ “እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤

5ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም ከንቱ ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፥ ወደ ጌልገላም አትግቡ፥ ወደ ቤርሳቤህም አትለፉ።”

6በዮሴፍ ቤት እሳት እንዳትቃጠል፥ በቤቴል የሚያጠፋትም ሳይኖር እንዳትበላ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።

7ፍርድን ወደ እሬት የምትለውጡ፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የምትጥሉ እናንተ ሆይ፥

8ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮን የተባለውን ኮከብ የፈጠረውን፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጠውን፥ ቀኑንም በሌሊት የሚያጨልመውን፥ የባሕሩንም ውኆች ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሳቸውን፥

9አምባውም እንዲፈርስ በብርቱ ላይ የድንገት ጥፋት የሚያመጣውን ፈልጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው።

10በበሩ አደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ።

11ድሀውንም ደብድባችኋልና፥ የስንዴውንም ቀረጥ ከእርሱ ወስዳችኋልና ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ሠርታችኋል፥ ነገር ግን አትቀመጡባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎች ተክላችኋል፥ ነገር ግን ከወይን ጠጃቸው አትጠጡም።

12ጻድቁን የምታስጨንቁ፥ ጉቦንም የምትቀበሉ፥ በበሩም አደባባይ የችጋረኛውን ፍርድ የምታጣምሙ እናንተ ሆይ፥ በደላችሁ እንዴት እንደ በዛ፥ ኃጢአታችሁም እንዴት እንደ ጸና እኔ አውቃለሁና።

13ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና በዚያ ዘመን አስተዋይ የሚሆን ዝም ይላል።

14በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ እንዲህም እናንተ እንደ ተናገራችሁ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል።

15ክፉውን ጥሉ፥ መልካሙንም ውደዱ፥ በበሩም አደባባይ ፍርድን አጽኑ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ቅሬታ ይራራ ይሆናል።

16ስለዚህ ጌታ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በየአደባባዩ ሁሉ ላይ ዋይታ ይሆናል፤ በየመንገዱም ሁሉ ላይ ወዮ ወዮ ይባላል፤ ገበሬዎቹም ወደ ልቅሶ፥ አልቃሾቹም ወደ ዋይታ ይጠራሉ።

17በመካከልህ አልፋለሁና በወይኑ ቦታ ሁሉ ልቅሶ ይሆናል፥” ይላል እግዚአብሔር።

18የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።

19ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው።

20የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?

21ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ ተጸይፌውማለሁ፤ የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም።

22የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም።

23የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም።

24ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ።

25የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ በምድረ በዳ አርባ ዓመት ሙሉ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኛልን?

26ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ምስሎች፥ የሞሎክን ድንኳንና የአምላካችሁን የሬፋን ኮከብ አነሣችሁ።

27ስለዚህ ከደማስቆ ወደዚያ አስማርካችኋለሁ፥ ይላል ስሙ የሠራዊት አምላክ የተባለ እግዚአብሔር።

ማብራሪያ

5:1-6 አሳማኝና የሚያነቃቃ ቃል መስማትና ማክበር ያስፈልጋል፤ እንደዚሁም የመጽናናትና የሰላም ቃላት። ብንሰማም ባንሰማም፣ የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል። ጌታ አሁንም ለሰዎች ምሕረትን ያውጃል፤ ነገር ግን እነርሱ ብዙ ጊዜ ፍርዳቸውን ከሚያረጋግጡላቸው በራሳቸው ፈጠራ ከሆኑ ሥርዓቶች መዳንን ይጠብቃሉ። ሕይወትን ለማግኘት ወደ ክርስቶስ መምጣት እና በእርሱም አማካኝነት ምሕረትን መፈለግ እምቢ ሲሉ፣ የመለኮታዊ ቁጣ እሳት በእነርሱ ላይ ይወርድባቸዋል። ሰዎች ዓለምን ጣዖት ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሊከላከልላቸው እንደማይችል ይገነዘባሉ።

ምዕራፍ 5:7-17

ያው ሁሉን ቻይ ኃይል ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች መከራንና ሐዘንን በቀላሉ ወደ ብልጽግናና ደስታ ሊለውጥ ይችላል፤ እንዲሁም የድፍረኞች ኃጢአተኞችን ብልጽግና በቀላሉ ወደ ጥልቅ ጨለማ ሊመልስ ይችላል። ክፉ ዘመናት ግልጽ አነጋገርን አይታገሡም፤ ይኸውም ክፉ ሰዎች አይታገሡም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6