1በኢዩ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች።
2ካህኑ ዮዳሄም ያስተምረው በነበረ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
3ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
4ኢዮአስም ካህናቱን፦ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገባውን የተቀደሰውን ገንዘብ ሁሉ፥ ስለ ነፍሱም ዋጋ የሚቀርበውን ገንዘብ፥ በልባቸውም ፈቃድ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚያመጡትን ገንዘብ ሁሉ፥
5ካህናቱ እያንዳንዱ ሰው ከሚያመጣው ይውሰዱ በመቅደስም ውስጥ የተናዱትን ይጠግኑበት፡ አላቸው።
6ነገር ግን እስከ ንጉሡ እስከ ኢዮአስ እስከ ሀያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ካህናቱ አልጠገኑትም ነበር።
7ኢዮአስም ካህኑን ዮዳሄንና ካህናቱን ጠርቶ፦ በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ስፍራዎች ስለ ምን አትጠግኑአቸውም? ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ ለቤቱ መጠገኛ ይሰጥ እንጂ ከሚያመጡት ሰዎች አትቀበሉ፡ አላቸው።
8ካህናቱም፦ ከሕዝቡ ገንዘቡን አንወስድም፥ በቤቱም ውስጥ የተናዱትን አንጠግንም፡ ብለው እሺ አሉ።
9ካህኑ ዮዳሄ ግን ሣጥን ወስዶ መክደኛውን ነደለው፥ በመሠዊያውም አጠገብ ወደ እግዚአብሔር ቤት በሚገቡበት መግቢያ በስተ ቀኝ አኖረው፤ ደጁንም የሚጠብቁ ካህናት ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ ሁሉ ያኖሩበት ነበር።
10በሣጥንም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን ባዩ ጊዜ የንጉሡ ጸሐፊና የካህናቱ አለቃ ይመጡ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ቈጥረው በከረጢት ውስጥ ያኖሩት ነበር።
11የተመዘነውንም ገንዘብ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት በተሾሙት እጅ ይሰጡ ነበር።
12የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመጠገን መክፈል ለሚያሻው ሁሉ ድንጋይና እንጨት ይገዙ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ አናጢዎችና ሠራተኞች ግንበኞችና ድንጋይ ወቃሪዎች ይሰጡት ነበር።
13ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ቤት ከሚመጣው ገንዘብ ለእግዚአብሔር ቤት የሚሆኑ የብር ጽዋዎችና ጕጠቶች ድስቶችም መለከቶችም የወርቅና የብር ዕቃዎችም አልተሠሩም ነበር።
14ነገር ግን ለሚሠሩት ይሰጡት ነበር፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ጠገኑበት።
15ለሠራተኞችም ይከፍሉ ዘንድ ገንዘቡን የሚወስዱትን ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር፤ በታማኝነት ይሠሩ ነበርና።
16ስለ በደልና ሰለ ኃጢአት መሥዋዕት የቀረበውም ገንዘብ ለካህናት ነበረ እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አያገቡትም ነበር።
17በዚያም ወራት የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጥቶ ጌትን ወጋ፥ ያዘውም፤ አዛሄልም ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት ፊቱን አቀና።
18የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአስ አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥና ኢዮራም አካዝያስም የቀደሱትን ቅዱስ ነገር፥ እርሱም የቀደሰውን፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ወሰደ፥ ወደ ሶርያም ንጉሥ ወደ አዛሄል ላከው። እርሱም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።
19የቀረውም የኢዮአስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
20ባሪያዎቹም ተነሥተው ዐመፁበት፥ ወደ ሲላ በሚወርደውም መንገድ በሚሎ ቤት ገደሉት።
21ባሪያዎቹም የሰምዓት ልጅ ዮዘካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት መቱት፥ ሞተም፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም አሜስያስ በፋንታው ነገሠ።