ኤልሳዕና ዘይት

37 ቁጥሮች2አማርኛ

2ኛ ነገ 4:1-7

1ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት፦ ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል፡ ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።

2ኤልሳዕም፦ አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ፡ አላት። እርስዋም፦ ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም፡ አለች።

3እርሱም፦ ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም፡ አላት።

4ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ፡ አለ።

5እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያመጡ ነበር፥ እርስዋም ትገለብጥ ነበር።

6ማድጋዎቹም በሞሉ ጊዜ ልጅዋን፦ ደግሞም ማድጋ አምጣልኝ አለችው፤ እርሱም፦ ሌላ ማድጋ የለም አላት፤ ዘይቱም ቆመ።

7መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም፦ ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ፥ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ፡ አለ።

2ኛ ነገ 4:8-37

8አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱነም አለፈ፥ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራ ይበላ ዘንድ የግድ አለችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር።

9ለባልዋም፦ ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ።

10ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል፡ አለችው።

11አንድ ቀንም ወደዚያ በመጣ ጊዜ ወደ ቤቱ ገብቶ በዚያ ዐረፈ።

12ሎሌውንም ግያዝን፦ ይህችን ሱነማዊት ጥራ፡ አለው።

13በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች። እርሱም፦ እነሆ፥ ይህን ሁሉ አሳብ አሰብሽልኝ፤ አሁንስ ምን ላድርግልሽ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን? በላት፡ አለው፤ እርስዋም፦ እኔ በወገኔ መካከል ተቀምጫለሁ፡ ብላ መለሰች።

14እርሱም፦ እንግዲህ ምን እናድርግላት? አለ። ግያዝም፦ ልጅ የላትም፤ ባልዋም ሸምግሎአል፡ ብሎ መለሰ።

15እርሱም፦ ጥራት፡ አለ። በጠራትም ጊዜ በደጃፉ ቆመች።

16እርሱም፦ በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ፡ አለ፤ እርስዋም፦ አይደለም ጌታዬ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ባሪያህን እንዳትዋሻት እለምንሃለሁ፡ አለች።

17ሴቲቱም ፀነሰች፥ በዚያም ወራት በአዲሱ ዓመት ኤልሳዕ እንዳላት ወንድ ልጅ ወለደች።

18ሕፃኑም አደገ፥ አንድ ቀንም እህል አጫጆች ወዳሉበት ወደ አባቱ ወጣ።

19አባቱንም፦ ራሴን ራሴን፡ አለው፤ እርሱም ሎሌውን፦ ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው፡ አለው።

20አንሥቶም ወደ እናቱ ወሰደው፤ በጕልበትዋም ላይ እስከ ቀትር ድረስ ተቀመጠ፥ ሞተም።

21ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አጋደመችው፥ በሩንም ዘግታበት ወጣች።

22ባልዋንም ጠርታ፦ ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እመለስ ዘንድ አንድ ሎሌና አንድ አህያ ላክልኝ፡ አለችው።

23እርሱም፦ መባቻ ወይም ሰንበት ያይደለ ዛሬ ለምን ትሄጂበታለሽ? አለ። እርስዋም፦ ደኅና ነው፡ አለች።

24አህያውንም አስጭና ሎሌዋን፦ ንዳ፥ ሂድ፤ እኔ ሳላዝዝህ አታዘግየኝ፡ አለችው።

25እንዲሁም ሄደች፥ ወደ እግዚአብሔርም ሰው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጣች። የእግዚአብሔርም ሰው ከሩቅ ባያት ጊዜ ሎሌውን ግያዝን፦ እነኋት ሱነማዊቲቱ መጣች፤

26ትቀበላትም ዘንድ ሩጥና፦ በደኅናሽ ነውን? ባልሽ ደኅና ነውን? ልጅሽስ ደኅና ነውን? በላት፡ አለው። እርስዋም፦ ደኅና ነው፡ አለች።

27ወደ ተራራው ወደ እግዚአብሔር ሰው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት ቀረበ፤ የእግዚአብሔርም ሰው፦ ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝምም፡ አለ።

28እርስዋም፦ በውኑ ከጌታዬ ልጅን ለመንሁን? እኔም፦ አታታልለኝ፡ አላልሁህምን? አለች።

29ግያዝንም፦ ወገብህን ታጠቅ፥ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሂድ፤ ሰውም ብታገኝ ሰላም አትበል፥ እርሱም ሰላም ቢልህ አትመልስለት፤ በትሬንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኑር፡ አለው።

30የሕፃኑም እናት፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! አልተውህም፡ አለች፤ ተነሥቶም ተከተላት።

31ግያዝም ቀደማቸው፥ በትሩንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኖረው፤ ነገር ግን ድምፅ ወይም መስማት አልነበረም፤ እርሱንም ሊገናኘው ተመልሶ፦ ሕፃኑ አልነቃም፡ ብሎ ነገረው።

32ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር።

33ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።

34መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ።

35ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ።

36ግያዝንም ጠርቶ፦ ይህችን ሱነማዊት ጥራ፡ አለው። ጠራትም፥ ወደ እርሱም በገባች ጊዜ፦ ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ፡ አላት።

37ገብታም በእግሩ አጠገብ ወደቀች፡ በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጅዋንም አንሥታ ወጣች።