ኤልያስ ወደ መንግሥተ ሰማያት ተወሰደ

18 ቁጥሮችአማርኛ

2ኛ ነገ 2:1-18

1እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ።

2ኤልያስም ኤልሳዕን፦ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ፡ አለው። ኤልሳዕም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም፡ አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ።

3በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፦ እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም፦ አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፡ አላቸው።

4ኤልያስም፦ ኤልሳዕ ሆይ፥ እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፡ አለው። እርሱም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም፡ አለ። ወደ ኢያሪኮም መጡ።

5በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው፦ እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም፦ አዎን አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፡ ብሎ መለሰ።

6ኤልያስም፦ እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፡ አለው። እርሱም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም፡ አለ። ሁለቱም ሄዱ።

7ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፥ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር።

8ኤልያስም መጐናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፥ ውኃውንም መታ፥ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ።

9ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፦ ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን፡ አለው፤ ኤልሳዕም፦ መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ፡ አለ።

10እርሱም፦ አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም፡ አለ።

11ሲሄዱም፥ እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።

12ኤልሳዕም አይቶ፦ አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፡ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።

13ከኤልያስም የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሣ፥ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ።

14ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውኃውን መታና፦ የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፤ ውኃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።

15ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ፦ የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል፡ አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ።

16እነርሱም፦ እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኃያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን፡ አሉት። እርሱም፦ አትስደዱ፡ አላቸው።

17እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ፦ ስደዱ፡ አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም።

18በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም፦ አትሂዱ አላልኋችሁምን? አላቸው።