ዳዊትና ዮናታን

32 ቁጥሮች2አማርኛ

1ኛ ሳሙ 18:6-30

6እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ።

7ሴቶችም፦ ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ፡ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር።

8ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፤ እርሱም፦ ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ።

9ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው።

10በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ። ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር።

11ሳኦልም፦ ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ፡ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ።

12እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።

13ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥ የሺህ አለቃም አደረገው፤ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር።

14ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።

15ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው።

16ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ።

17ሳኦልም ዳዊትን፦ ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርስዋን እድርልሃለሁ፤ ብቻ ቀልጣፋ ልጅ ሁንልኝ፥ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል፡ አለው። ሳኦልም፦ የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን፡ ይል ነበር።

18ዳዊትም ሳኦልን፦ ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድር ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድር ነው? አለው።

19ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች።

20የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፤ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፥ ነገሩም ደስ አሰኘው።

21ሳኦልም፦ ወጥመድ ትሆነው ዘንድ፥ የፍልስጥኤማውያንም እጅ በእርሱ ላይ ትሆን ዘንድ እርስዋን እድርለታለሁ አለ፤ ሳኦልም ዳዊትን፦ ዛሬ ሁለተኛ አማች ትሆነኛለህ፡ አለው።

22ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ እነሆ፥ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ወድደውሃል፥ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን፡ ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት ብሎ አዘዛቸው።

23የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፤ ዳዊትም፦ እኔ ድሀ የተጠቃሁም ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን? አለ።

24የሳኦልም ባሪያዎች፦ ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ፡ ብለው ነገሩት።

25ሳኦልም ዳዊትን በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ፦ የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም፡ ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት፡ አላቸው።

26የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፥ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው።

27ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ሁለት መቶ ሰዎች ገደሉ፤ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቍጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት።

28ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፤ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት።

29ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፤ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ።

30የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፤ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል ባሪያዎች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።

1ኛ ሳሙ 19:1-7

1ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር።

2ዮናታንም፦ አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፤

3እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፤ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው።

4ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል፦ እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤

5ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ፤ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ።

6ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም፡ ብሎ ማለ።

7ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፤ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ።