ሰዶምና ገሞራ

47 ቁጥሮች2አማርኛ

ዘፍ 18:16-33

16ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ።

17እግዚአብሔርም አለ፦ “እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን?

18አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና።

19ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፤ ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው።”

20እግዚአብሔርም አለ፦ “የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥

21እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ።”

22ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር።

23አብርሃምም ቀረበ አለም፦ “በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን?

24አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን?

25ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?”

26እግዚአብሔርም፦ “በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ፡” አለ።

27አብርሃምም መለሰ አለም፦ “እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤

28ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን?” “ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም፡” አለ።

29ደግሞም ተናገረው፥ እንዲህም አለ፦ “ምናልባት ከዚያ አርባ ቢገኙሳ?” እርሱም፦ “ለአርባው ስል አላደርገውም፡” አለ።

30እርሱም፦ “ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ፡ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም፡” አለ።

31ደግሞም፦ “እነሆ፥ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ ምናልባት ከዚያ ሀያ ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ከዚያ ሀያ ቢገኙ ስለ ሀያው አላደርገውም፡” አለ።

32እርሱም፦ “እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ?” አለ። እርሱም፦ “ስለ አሥሩ አላጠፋትም፡” አለ።

33እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ።

ዘፍ 19:1-29

1ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥

2አላቸውም፦ “ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ።” እነርሱም፦ “በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም፡” አሉት።

3እጅግም ዘበዘባቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ።

4ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት።

5ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት፦ “በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው።”

6ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው፤

7እንዲህም አለ፦ “ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ፤

8እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው፤ በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬ ጥላ ሥር ገብተዋልና።”

9እነርሱም፦ “ወዲያ ሂድ፡” አሉት። ደግሞም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል፤ አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን።” ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ።

10ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት።

11በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው፤ ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።

12ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት፦ “ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፤

13እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል።”

14ሎጥም ወጣ፥ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም ነገራቸው፥ አላቸውም፦ “ተነሡ፤ ከዚህ ስፍራ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋልና።” ለአማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው።

15ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፦ “ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ” እያሉ ያስቸኵሉት ነበር።

16እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት።

17ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው፦ “ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም፡ እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።”

18ሎጥም፤ አላቸው፦ “ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፤

19እነሆ ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፤ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፤

20እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ፤ እርስዋ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?”

21እርሱም አለው፦ “የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፤

22በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ።

23ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች።

24እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤

25እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ።

26የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች።

27አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤

28ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ።

29እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፤ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው።