ሰሎሞን እና ሳባ

12 ቁጥሮችአማርኛ

2ኛ ዜና 9:1-12

1የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቱና ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤ ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው።

2ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሰሎሞንም ያልፈታው ስውር ነገር አልነበረም።

3የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ የማዕዱንም መብል፥

4የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም አለባበሳቸውንም በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ መንፈስ አልቀረላትም።

5ንጉሡንም አለችው፦ ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው።

6እኔ ግን መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም፤ እነሆ፥ የጥበብህን ታላቅነት እኵሌታ አልነገሩኝም፤ ከሰማሁት ዝና ትበልጣለህ።

7በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው።

8በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደህ አምላክህ እግዚአብሔር ብሩክ ይሁን፤ አምላክህ እስራኤልን ለዘላለም ያጸናቸው ዘንድ ወድዶአቸዋልና ስለዚህ ፍርድና ጽድቅ ታደርግ ዘንድ በላያቸው አነገሠህ።

9ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ፥ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ ሽቱ ከቶ አልነበረም።

10ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም ባሪያዎችና የሰሎሞን ባሪያዎች የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ደግሞ አመጡ።

11ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት ደርብ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም ነበር።

12የሳባም ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው የሚበልጥ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች።