ኖኅና መርከብ

59 ቁጥሮች4አማርኛ

ዘፍ 6:9-22

9የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።

10ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።

11ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች።

12እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና።

13እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፦ “የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።

14ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ጉርጆችን አድርግ፥ በውስጥም በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት።

15እርስዋንም እንዲህ ታደርጋታለህ፤ የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ ይሁን።

16ለመርከቢቱም መስኮትን ታደርጋለህ፤ ከቁመትዋም ክንድ ሙሉ ትተህ ጨርሳት፤ የመርከቢቱንም በር በጎንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም ሁለተኛውንም ሦስተኛውንም ደርብ ታደርግላታለህ።

17እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል።

18ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አቆማለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ።

19ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን።

20ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ።

21ከሚበላውም መብል ሁሉ ለአንተ ውሰድ፥ ወደ አንተም ትሰበስባለህ፤ እርሱም ለአንተም ለእነርሱም መብል ይሆናል።”

22ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።

ዘፍ 7:1-24

1እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፦ “አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።

4ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ አጠፉለሁና።”

5ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ።

6ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ።

7ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ።

8ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥

9እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።

10ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ።

11በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፥ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤

12ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ።

13በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም ካም ያፌትና የኖኅ ሚስት ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ገቡ።

14እነርሱ፥ አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥

15ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።

16ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ እግዚአብሔርም በስተ ኋላው ዘጋበት።

17የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን ነበረ፤ ውኃውም በዛ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች።

18ውኃውም አሸነፈ፥ በምድር ላይም እጅግ በዛ፤ መርከቢቱም በውኃ ላይ ሄደች።

19ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፤ ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ።

20ውኃው ወደ ላይ አሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ፤ ተራሮችም ተሸፈኑ።

21በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ ወፉም፥ እንስሳውም፥ አራዊቱም፥ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሹም ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ጠፋ።

22በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ።

23በምድር ላይ የነበረውም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ፥ እስከሚርመሰመሰውም ሁሉ ድረስ፥ እስከ ሰማይ ወፍ ድረስ ተደመሰሰ፤ ከምድርም ተደመሰሱ። ኖኅም አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ።

24ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ አሸነፈ።

ዘፍ 8:1-22

1እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ አሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አሳለፈ፥ ውኃውም ጎደለ፤

2የቀላዩም ምንጮች የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፥ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤

3ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ።

4መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች።

5ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበር፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ራሶች ተገለጡ።

6ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥

7ቁራንም ሰደደው፤ እርሱም ወጣ፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር።

8ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ቀልሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ ዘንድ ሰደዳት።

9ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች፥ ውኃ በምድር ላይ ሁሉ ስለ ነበረ፤ እጁን ዘረጋና ተቀበላት፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት።

10ከዚያም በኋላ ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም እንደ ገና ከመርከብ ሰደደ።

11ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ።

12ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም ሰደዳት ዳግመኛም ወደ እርሱ አልተመለሰችም።

13በኖኅ ዕድሜ በስድስት መቶ አንድ ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅም የመርከቢቱን ክዳን አነሣ፥ እነሆም፥ ውኃው ከምድር ፊት እንደ ደረቀ አየ።

14በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ደረቀች።

15እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ ብሎ ነገረው፦

16“አንተ ሚስትህንና ልጆችህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ከመርከብ ውጣ።

17ከአንተ ጋር ያሉትን አራዊት ሁሉ፥ ሥጋ ያላቸውን ሁሉ፥ ወፎችንና እንስሶችን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ከአንተ ጋር አውጣቸው፤ በምድር ላይ ይርመስመሱ፥ ይዋለዱ፥ በምድርም ላይ ይብዙ።”

18ኖኅም ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወጣ፤

19አራዊት ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ ወፎችም ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚርመሰምሰው ሁሉ በየዘመዳቸው ከመርከብ ወጡ።

20ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፥ ከንጹሕም እንስሳ ሁሉ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፥ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ።

21እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ፦ “ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም።

22በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።”

ዘፍ 9:17

17እግዚአብሔርም ኖኅን፦ “በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፡” አለው።