ዮሐንስ በእስር ቤት ውስጥ አስገባ
31 ቁጥሮች3አማርኛማር 6:14-20
14ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል፡ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል፡” አለ።
15ሌሎችም፦ “ኤልያስ ነው” አሉ፤ ሌሎችም፦ “ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” አሉ።
16ሄሮድስ ግን ሰምቶ፦ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፡” አለ።
17ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤
18ዮሐንስ ሄሮድስን፦ “የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም፡” ይለው ነበርና።
19ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤
20ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ በደስታም ይሰማው ነበር።
ማር 6:21-29
21ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና፥
22የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን፦ “የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ፡” አላት፤
23የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ፡ ብሎ ማለላት።
24ወጥታም ለእናትዋ፦ “ምን ልለምነው?” አለች። እርስዋም፦ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” አለች።
25ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ፡” ብላ ለመነችው።
26ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም።
27ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥
28ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች።
29ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።
ማር 6:30-44
30ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት።
31እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ።
32በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ።
33ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ።
34ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።
35በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤
36የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው፡” አሉት።
37እርሱ ግን መልሶ፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው። “ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን?” አሉት።
38እርሱም፦ “ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ” አላቸው። ባወቁም ጊዜ፦ “አምስት፥ ሁለትም ዓሣ” አሉት።
39ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው።
40መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ።
41አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥
42ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤
43ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ።
44እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ።