ዮናስ እና ዓሣ ነባሪ
27 ቁጥሮች2አማርኛዮና 1:1-17
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፦
2“ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።”
3ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኰበልል ዘንድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አገኘ፤ ከእግዚአብሔርም ፊት ኰብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርስዋ ገባ።
4እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣ፥ በባሕርም ላይ ታላቅ ማዕበል ሆነ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች።
5መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱም እንድትቀልልላቸው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ውስጠኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር።
6የመርከቡም አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ፡” አለው።
7እርስ በእርሳቸውም፦ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ፥ ዕጣ እንጣጣል፡” ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፥ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ።
8የዚያን ጊዜም፦ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ?” አሉት።
9እርሱም፦ “እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ፡” አላቸው።
10እነዚያም ሰዎች ከእግዚአብሔር ፊት እንደ ኰበለለ እርሱ ስለ ነገራቸው አውቀዋልና እጅግ ፈርተው፦ “ይህ ያደረግኸው ምንድር ነው?” አሉት።
11ባሕሩንም ሞገዱ አጥብቆ ያናውጠው ነበርና፦ “ባሕሩ ከእኛ ዘንድ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ?” አሉት።
12እርሱም፦ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፡” አላቸው።
13ሰዎቹ ግን ወደ ምድሩ ሊመለሱ አጥብቀው ቀዘፉ፤ ዳሩ ግን ባሕሩ እጅግ አብዝቶ ይናወጥባቸው ነበርና አልቻሉም።
14ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው፦ “አቤቱ፥ እንደ ወደድህ አድርገሃልና እንለምንሃለን፤ አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን፡” አሉ።
15ዮናስንም ወስደው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም ከመናወጡ ጸጥ አለ።
16ሰዎችም እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፥ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕትን አቀረቡ፥ ስእለትንም ተሳሉ።
17እግዚአብሔርም ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ነበረ።
ዮና 2:1-10
1ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እንዲህም አለ፦
2“በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ።
3ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ፥ ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ።
4እኔም፦ ‘ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፤ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁ፡’ አልሁ።
5ውኆችም እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ፤ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር።
6ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፤ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ ለዘላለም ተዘጋሁ፤ አንተ ግን፥ አቤቱ አምላኬ፥ ሕይወቴን ከጕድጓዱ አወጣህ።
7ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብሁት፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች።
8ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ ምሕረታቸውን ትተዋል።
9እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።”
10እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፥ እርሱም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው።