ዮሴፍ ግብፅን ገዛ

13 ቁጥሮችአማርኛ

ዘፍ 41:37-49

37ነገሩም በፈርዖንና በሎሌዎቹ ፊት መልካም ሆነ፤

38ፈርዖንም ሎሌዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን እንደዚህ ያለ ሰው እናገኛለንን?”

39ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ “እንደ አንተ ያለ ብልህ አዋቂም ሰው የለም፥ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና።

40አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፥ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ።”

41ፈርዖንም ዮሴፍን፦ “በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾምሁህ፡” አለው።

42ፈርዖን ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ በዮሴፍ እጅም አደረገው፥ ነጭ የተልባ እግር ልብስንም አለበሰው፥ በአንገቱም የወርቅ ዝርግፍን አደረገለት፤

43የእርሱም በምትሆን በሁለተኛይቱ ሰረገላ አስቀመጠው፥ አዋጅ ነጋሪም፦ “ስገዱ፡” እያለ በፊት በፊቱ ይጮኽ ነበር፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ተሾመ።

44ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ በግብፅ አገር ሁሉ ያለ አንተ ማንም እጁንም እግሩንም አያንሣ።”

45ፈርዖንም የዮሴፍን ስም ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ጠራው፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ የምትሆን አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በግብፅ ምድር ሁሉ ወጣ።

46ዮሴፍም በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊት በቆመ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ የግብፅ ምድርንም ሁሉ ዞረ።

47በሰባቱም በጥጋብ ዓመታት የምድሪቱ ፍሬ ክምር ሆነ።

48በግብፅ ምድር ሁሉ ያለውን የሰባቱን ዓመት እህል ሁሉ ሰበሰበ፥ እህልንም በከተሞቹ አደለበ፤ በየከተማይቱ ዙሪያ ያለውን የእርሻውን እህል ሁሉ በዚያው ከተተ።

49ዮሴፍም እንደ ባሕር አሸዋ እጅግ ብዙ የሆነ ስንዴን አከማቸ፥ መስፈርን እስኪተው ድረስ፤ ሊሰፈር አልተቻለምና።