ኢየሱስ እየሩሳሌምን ተናገረ
21 ቁጥሮች2አማርኛማር 10:32-45
32ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር፦
33“እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥
34ይዘብቱበትማል፡ ይተፉበትማል፡ ይገርፉትማል፡ ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፡” አላቸው
35የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው፦ “መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን” አሉት።
36እርሱም፦ “ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ?” አላቸው።
37እነርሱም፦ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን፡” አሉት።
38ኢየሱስ ግን፦ “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው።
39እነርሱም፦ “እንችላለን፡” አሉት። ኢየሱስም፦ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤
40በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም፡” አላቸው።
41አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር።
42ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።
43በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥
44ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤
45እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”
ማር 10:46-52
46ወደ ኢያሪኮም መጡ። ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር።
47የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ፦ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ፡” እያለ ይጮኽ ጀመር።
48ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፦ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ፡” እያለ አብዝቶ ጮኸ።
49ኢየሱስም ቆመና፦ “ጥሩት” አለ። ዕውሩንም፦ “አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል” ብለው ጠሩት።
50እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ።
51ኢየሱስም መልሶ፦ “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?” አለው። ዕውሩም፦ “መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ፡” አለው።
52ኢየሱስም፦ “ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፡” አለው። ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው።